Sunday, September 22, 2024
spot_img

ባልደራስ ባካሔደው የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ስብሰባ ከ45 አባላት መካከል የተገኙት 7 ብቻ ነው ተባለ

አምባ ዲጂታል፤ ዐርብ መስከረም 20፣ 2015 በቅርቡ መስራቹ እና ሊቀመንበሩ አቶ እስክንድር ነጋ የለቀቁበት ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ)፤ በነሐሴ ወር አጋማሽ ባካሄደው የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ስብሰባ ከ45 አባላት መካከል የተገኙት 7 ብቻ መሆናቸውን ያስታወቀው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው ፓርቲው መስከረም 29፣ 2015 አካሄደዋለሁ ያለውን ጠቅላላ ጉባዔ አስመልክቶ ያስገባውን ሠነድ መርምሬ ሕጉንና የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ የተከተለ ሆኖ ስላላገኘሁት ውድቅ አድርጌዋለሁ ባለበት ደብዳቤ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ‹‹የመጀመሪያው ቀኝ ዘመም›› ፓርቲ መሆኑን የሚገልጸው ባልደራስ በአወዛጋቢው የቀድሞ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የተመሠረተው ጥር 3፣ 2012 ነበር፡፡

ሆኖም የድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በዚያው ዓመት ከሰኔ አንስቶ እስከ ታኅሣሥ 29፣ 2014 ድረስ በእስር ያሳለፉት አቶ እስክንድር፤ በራሳቸው እጅ ሐምሌ 16፣ 2014 በተጻፈ ደብዳቤ ፓርቲውን መምራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን አሳውቀው ከአደባባይ ተሰውረዋል፡፡ አቶ እስክንድር ለውሳኔው ሰበብ የሆናቸው ‹‹ተረኛው ጨቋኝ›› ያሉት መንግሥት በፓርቲያቸውም ሆነ ‹‹በአገር አቀፍ ደረጃ በፈጠረው የለየለት አምባገነናዊ ጫና›› መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ እስክንድር ከፓርቲው መልቀቃቸውን በገለጹበት ደብዳቤ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ አባላት፣ በየደረጃው ያሉ የፓርቲው አመራር አባላት፣ መላ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ከፓርቲው ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አምሃ ዳኘው ጋር ሙሉ ለሙሉ በመተባበር ስራቸው የተቃና እንዲሆን እንድትተባበሯቸው ሲሉ ጠይቀው ነበር፡፡

ባልደራስ በእኚሁ ምክትል ፕሬዝዳንት ነሐሴ 21፣ 2014 በተፈረመ ደብዳቤ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ነሐሴ 15፣ 2014 መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ ያልተሟሉ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን ማሟላቱን እንዲሁም ነሐሴ 23፣ 2014 በተፃፈ ደብዳቤ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት መስከረም 29፣ 2015 ጠቅላላ ጉባኤ እንዲደረግ መወሰኑን ለምርጫ ቦርድ አሳውቋል፡፡

ይሁንና ብሔራዊ ምክር ቤቱ ነሐሴ 15 ተሰብስቦ የስራ አስፈፃሚ አባላትን ማፅደቁ እና የጠቅላላ ጉባኤ ቀን ወስኗል በሚል በቀረበው ቃለ ጉባኤ 12 አባላት እንደተሰበሰቡ፤ ይህም የሆነው ሁለት ጊዜ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ስብሰባ ተጠርቶ ምልዓተ ጉባኤ ባለመሟላቱ ምክንያት እንደሆነ በመግለፅ ስብሰባውን እንደቀጠሉ የተገለጸ ቢሆንም፤ በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል ከተባሉት የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት መካከል ምርጫ ቦርዱ እውቅና ከሰጣቸው 45 የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት መካከል የተገኙት 7 ብቻ ናቸው መሆኑ ተገልጧል፡፡

ምርጫ ቦርድ እንዳሳወቀው ከሆነ የቀረበው ሰነድ ብሔራዊ ምክር ቤቱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በወሰነው ቦታና ጊዜ ሁለት ጊዜ ተጠርቶ እንደነበር እና ምልዓተ ጉባኤውም በሁለቱ የተጠሩ ስብሰባዎች ያልተሟላ የነበረ ስለመሆኑ አያሳይም፡፡ በዚሁ መሠረት በተጠቀሰው ቀን የብሔራዊ ምክር ቤቱ አካሂዶታል የተባለውን ስብሰባ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሎታል፡፡

በተጨማሪም የፓርቲው ፕሬዚዳንት የመረጧቸው ስራ አስፈፃሚዎች የፀደቁ ስለመሆኑ የሚያሳይ ማረጋገጫ አልቀረበም ያለው ምርጫ ቦርድ፤ ብሔራዊ ምክር ቤቱ አሳልፎታል የተባለውን ውሳኔም እንዲሁ ተቀባይነት እንዳላገኘ አመልክቷል፡፡ ቦርዱ የጠቅላላ ጉባኤ ቀን መወሰንን በተመለከተም በ12 የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ተደረገ የተባለው ስብሰባ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ተከትሎ የተካሄደ ባለመሆኑ መስከረም 29 ይካሄዳል የተባለውን ጠቅላላ ጉባኤ ውድቅ በማድረግ ጉባኤው ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ታዛቢ እንደማይልክ አሳውቋል፡፡  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባልደራስ ሊያካሄድ ያቀደውን የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ውድቅ ማድጉን በተመለከተ የፓርቲውን ውሳኔ ለማወቅ አምባ ዲጂታል የባልደራስ ሕዝብ ግንኙነት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ የእጅ ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img