Thursday, November 14, 2024
spot_img

ዳንጎቴን ጨምሮ ሰባት የሲሚንቶ አምራቾች አዲሱን የመሸጫ ዋጋ ተቃውመው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብደቤ ማስገባታቸው ተሰማ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ መስከረም 11 2015 ― የናይጄሪያው ባለሐብት የአሊኮ ዳንጎቴ ንብረት የሆነው ዳንጎቴ ሲሚንቶን ጨምሮ ሐበሻ፣ ናሽናልና ኢትዮ ሲሚንቶ ያሉበት የሰባት አምራቾች ቡድን መስከረም 4፣ 2015 የወጣውን ሲሚንቶ የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ ውሳኔን በመቃወም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቅሬታ ደብዳቤ ማስገባታቸው ተሰምቷል፡፡

ሚኒስቴሩ ከመስከረም 5፣ 2015 ጀምሮ ለሦስት ወራት ይቆያል ባለው የፋብሪካ ዋጋ ሁሉም ፋብሪካዎች ቀድሞ ሲሸጡበት ሲሸጡበት ከነበረው ዋጋ በኩንታል በአማካይ 92 ብር ዝቅ እንዲል አድርጓል፡፡

ውሳኔውን ተከትሎ የመከረው የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር በተገኙት ሰባት አባላት ቃለ ጉባዔው ላይ በመፈረም ተቃውሞውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገብቷል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ ሌሎች የማኅበሩ አባል የሆኑት ደርባ፣ ሙገር፣ ዳሸን፣ ካፒታልና ፓዬኔር የተሰኙ ሲሚንቶ አምራቾች እንዳልተገኙ የሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢ አቶ መስፍን አበራ ተፈርሞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላከው ደብዳቤ፣ በጉባዔው የተነሱትን የዋጋ ተመኑን አካሄድ የሚመለከት አምስት ዋነኛ የማኅበሩን ቅሬታዎች ያነሳል ነው የተባለው፡፡

ከቅሬታዎቹም መካከል የዋጋ ተመኑ ሲወጣ ፋብሪካዎች ያሉበትን የቦታና የግብዓት አቅርቦት ርቀት አለመረዳት፣ የግብዓት ዋጋ በየጊዜው መናርን በተገቢው ግምት አለማስገባትና እያንዳንዳቸው ፋብሪካዎች ያለባቸውን እንደ ኃይልና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዓይነት ልዩነት ያላቸው ወጪዎችን በአንድ ወጪ ቀመር መሣል ናቸው፡፡ በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች በመንግሥትና በባለሀብቱ መካከል ቅሬታን ይፈጥራል ሲልም ደብዳቤው ይገልጻል፡፡

ባለፈው ሳምንት የተወሰነው ይህ ውሳኔ ኢትዮ ሲሚንቶና ኢስት ሲሚንቶ በእኩል ዋጋ ኩንታል በ595.66 ብር እንዲሸጡ፣ ከፍተኛዎቹ ዋጋዎች ደግሞ ሐበሻ በ683.44 ብር፣ ሙገር በ643.95 ብር፣ ካፒታል በ633.38 ብርና ኩዩ በ628.10 ብር በእንዲሸጡ ያዛል፡፡ በሌላው ደረጃ ደግሞ ከዝቅተኛ ጀምሮ ፓዮኔር ኩንታል በ510.04 ብር፣ ዳንጎቴ በ549.49 ብር፣ ናሽናል በ561.39 ብርና ደርባ በ590.59 ብር እንዲሸጡ ያዛል፡፡

ሁሉም አምራቾች ካለፈው መጋቢት 2014 በፊት ይሸጡበት የነበረው ዋጋ ኩንታል ከ407 ብር እስከ ትልቁ 520 ብር ይሸጡ የነበረ ሲሆን፣ በዚያን ጊዜ ባደረጉት ጭማሪ ኩንታል ከትንሹ 620 ብር እስከ 790 ብር ይሸጡ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ እንዲሸጡ ባወጣው ትዕዛዝ መሠረት ግን ሲሸጡበት የነበሩበትን ዋጋዎች በአማካይ ኩንታል በ92.27 ብር ዝቅ ያደርገዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img