Tuesday, December 3, 2024
spot_img

ሱዳን በአገሯ የሚገኙትን የኢትዮጵያ አምባሳደር መጥራቷ ተዘገበ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ነሐሴ 25 2014 ጎረቤት ሱዳን በአገሯ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮን ጠርታለች የተባለው ከሰሞኑ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከሱዳን በኩል የጦር መሣሪያ ጭኖ ወደ ትግራይ ክልል ሲገባ መትቼ ጥዬዋለሁ ካለው አውሮፕላን ጋር በተገናኘ ነው፡፡

ሱዳን ትሪቡን እንደዘገበው፤ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ሰኞ ነሐሴ 23፣ 2014 ከአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ጉዳዩ የተናገሩት የአገሪቱን ሹማምንት አስቆጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የዘመቻዎች ዋና መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ነሐሴ 18፣ 2014 ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሱዳን አልፎ ለሕወሓት የጦር መሣሪያ በመጫን የኢትዮጵያ አየር ክልልን ጥሶ የገባ አንድ አውሮፕላን መትቶ መጣሉን ገልጸዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፤ ከሱዳን በኩል የጦር መሣሪያ ጭኖ ወደ ትግራይ ክልል ሲገባ ተመትቶ ተጥሏል ያሉት አውሮፕላን ሩስያ ሠራሹ አንቶኖቭ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ጀነራሉ አውሮፕላኑ ‹‹ፍቃድ ያልተሰጠው እና በተከለከለ የበረራ መስመር በኩል የገባ›› እንደነበርም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ማብራሪያ ተከትሎ የሱዳን ጦር ሠራዊት ኢትዮጵያ በአገሪቱ በኩል ጦር መሣሪያ ጭኖ ወደ ትግራይ ሲገባ መትቼ ጣልኩ ካለችው ክስተት ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም ሲል በቃል አቀባዩ በኩል ለአሜሪካው ብሉምበርግ በሰጠው ቃል አስተባብሏል፡፡

በአውሮፕላኑ የጦር መሣሪያ ሊጓጓዝለት ነበር የተባለው ሕወሃትም በቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ በኩል በተመሳሳይ የመንግሥትን መረጃ ‹‹ሐሰት ነው›› ብሎታል፡፡

አሁን በአምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ንግግር ተቆጥቷል የተባለው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የቀረበውን ክስ ‹‹መሠረተ ቢስ›› በማለት ያጣጣለው ሲሆን፣ አምባሳደሩ ጉዳዩን ለመገናኛ ብዙኃን መናገራቸውንም ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን የጣሰ ነው ብሎታል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ አየር ኃይል መረጃ መትቼዋለሁ ያለው አውሮፕላን በኢትዮጵያ አየር ክልል ውስጥ ተመትቶ የወደቀው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ኘሐሴ 17፣ 2014 ምሽት ሦስት ሰዓት ላይ ነው፡፡ ሶቪዬት ኅብረት ሠራሽ የሆነ አንቶኖቭ-26 40 ወታደሮችን ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው የመጫን አቅም አለው ተብሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img