Thursday, November 21, 2024
spot_img

ኢትዮጵያ ከአጎዋ በመታገዷ ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ከአምስት ሺሕ ሠራተኞች ተሰናበቱ

አምባ ዲጂታል፤ እሑድ ነሐሴ 22፣ 2014 ― የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ከአጎዋ (የአፍሪካ ነፃ የገበያ ዕድል) ተጠቃሚነት ማገዱን ተከትሎ ምርታቸውን ወደ አሜሪካ ሲልኩ የነበሩ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ አምራቾች በገበያ ዕጦት ያሰናበቷቸው ሠራተኞች ቁጥር ከአምስት ሺሕ በላይ ማለፉ ተገልጿል።

ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ኢትዮጵያ የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚ እንዳትሆን በአሜሪካ መንግሥት ዕገዳ ከተጣለባት ወዲህ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ አምስት የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች በገጠማቸው የገበያ ዕጦት ሠራተኞችን መቀነሳቸውንና በመቀነስ ላይ ይገኛሉ፡፡

በአጎዋ ዕድል ተጠቅመው ወደ አሜሪካ ከቀረጥ ነፃ ምርቶቻቸውን ሲያስገቡ ከነበሩ ኩባንያዎች ውስጥ ሁለቱ ሙሉ በሙሉ ሥራ ያቆሙና ሠራተኞቻቸውን ያሰናበቱ ሲሆን ሦስቱ ደግሞ ሠራተኞቻቸውን ቀንሰው ከማምረት አቅማቸው በታች እያመረቱ ይገኛሉ።

ሙሉ በሙሉ ሥራ ካቆሙት ኩባንያዎች ውስጥ ፒቪኤች 1,400 እና ቻርቸርስ 22 ሠራተኞች ነበሯቸው፡፡ ቤስት፣ ኤፔክና ኳድራንት የተባሉት ኩባንያዎች ደግሞ ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ባያቆሙም እንደ ቅደም ተከተላቸው 3,000፣ 1,200 እና 161 ሠራተኞች እንደቀነሱ ሪፖርተር ጋዜጣ መረጃውን ጠቅሶ ዘግቧል።

ከኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳትና የመሳሰሉት ሠራተኞች ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ያገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተውም፣ ከአጎዋ ተጠቃሚነት ዕገዳ በኋላ በተለይ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች ችግር ውስጥ መሆናቸውንና አማራጭ ገበያ በማጣታቸው ተጨማሪ ሠራተኞች ሊቀነሱ ይችላሉ የሚል ሥጋት አይሏል፡፡ 

ከገበያ ዕጦት ጋር በተያያዘ እነዚህ ኩባንያዎች በአሜሪካ መንግሥት የተጣለው ክልከላ ካልተነሳ ወይም አዲስ ገበያ የማያገኙ ከሆነ ተጨማሪ የሠራተኞች ቅነሳ ሊያደርጉ የሚችሉ መሆኑንም የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አንገሶም ገብረ ዮሐንስ ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ለዚህም እንደማሳያ ኤፔክ የተባለው ኩባንያ ተጨማሪ 100 ሠራተኞች ለመቀነስ እንደሚችል በዚህ ሳምንት ማስታወቁን ጠቁመዋል፡፡ አንፑቺንና ሔላ ሱብሪን የተባሉት ሁለት ኩባንያዎች ደግሞ 400 ለሚደርሱ ሠራተኞቻቸው ከክፍያ ጋር አስገዳጅ የዓመት ፈቃድ መስጠታቸውን ጠቅሰው፣ ይህም በቀጣይ ምን ሊከተል እንደሚችል አመላካች መሆኑን ገልጸዋል። 

ይህ አካሄድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን የሥራ ዋስትና እያሳጣ በመሆኑ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነባቸው የገለጹት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት  ኮንፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንድትወጣ በመደረጉ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ወደ ስድስት ሺሕ የሚጠጉ ሠራተኞች ሥራ ማሳጣቱን ገልጸዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img