Sunday, September 22, 2024
spot_img

አቶ እስክንድር ነጋ ወደ ትጥቅ ትግል ይገባሉ ብለው እንደማያምኑ የባልደራስ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፤ ዐርብ ነሐሴ 6፣ 2014 ― የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ በፓርቲው አመራርነት እንዲሁም አባልነት መሥራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ መጻፋቸውን ትላንት ነሐሴ 5፣ 2014 ባልደራስ ማሳወቁ የሚታወቅ ነው።

በፕሬዝዳንቱ እጅ ሐምሌ 16 በተጻፈው ደብዳቤ፤ አቶ እስክንድር ለውሳኔው ሰበብ የሆናቸው ‹‹ተረኛው ጨቋኝ›› ያሉት መንግሥት በፓርቲያቸውም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ በፈጠረው ‹‹የለየለት አምባገነናዊ ጫና›› መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንኑ ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች አቶ እስክንድር በዘመነ ካሴ የሚመራውን ፋኖ የተሠኘውን መደበኛ ያልሆነ አደረጃጀት ተቀላቅለዋል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

ጉዳዩን በተመለከተ ባልደራስ ፓርቲ የሚያውቀው ነገር እንዳለ ለማወቅ አምባ ዲጂታል የፓርቲውን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር በቃሉን አነጋግሯል።

ኃላፊው ዜናውን የሰሙት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ “አሉባልታ ነው ብለን እናስባለን” ሲሉ መልሰዋል። “አቶ እስክንድር ነጋ ለሰላማዊ ትግል ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ ወደ ትጥቅ ትግል ይገባሉ ብለን አናምንም” ሲሉ አክለዋል።

አቶ እስክንድር ነጋ ከባልደራስ ጋር የነበራቸው ግንኙነት የተቋረጠው ሐምሌ 16 በፓርቲው ቢሮ ውስጥ ከተካሄደው ስብሰባ ከተካፈሉ በኋላ መሆኑንም ተናግረዋል።

ስለ ስብሰባው ያስታወሱት የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት፣ አቶ እስክንድር በስብሰባው ወቅት ከፓርቲው እንደሚለቁ እንዳላሳወቁ ተናግረዋል። ሆኖም ከስብስባው በኋላ ስልክ እንደማይመልሱና ቢሮ መግባት እንዳቆሙ ገልፀዋል።

ቀድሞ በጋዜጣ ባለቤትነትና ጸሐፊነት የሚታወቁት አቶ እስክንድር ነጋ፣ የሐጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ታስረው ከተፈቱ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አሜሪካ በመሄድ ከቤተሰቦቻቸውና ከደጋፊዎቻቸው ጋር መገናኘታቸው ይታወቃል፡፡ ፓርቲውንም ከክልል ፓርቲነት ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት ለማሸጋገር የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ጀምረው ነበር፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በእንጥልጥል ባለበት ነው ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን መልቀቃቸውን ያሳወቁት፡፡

የሕዝብ ግንኙነቱ ቀጣይ የፓርቲውን እጣ ፋንታ በተመለከተ ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‘’አቶ እስክንድርን የሚተካ ፕሬዝዳንት ለመምረጥና ቀጣይ አካሄዳችንን ለመወሰን የነባር ጠቅላላ ጉባኤ አባላት የሚሳተፉበት ጉባኤ ጠርተናል” ብለዋል። ቀኑ ነሐሴ 22፣ 2014 ይሆናል ብለው እንደሚጠብቁም አመልክተዋል። በጉባኤው ላይም ሀገር አቀፍ ፓርቲ የምሆን ሂደት ላይ ውሳኔ እናስተላልፋለን የሚል እቅድ ይዘናል ሲሉ አክለዋል።

አቶ እስክንድር ቢሮ መምጣት ካቆሙ በኋላ ግንኙነታቸው በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የባልደራስ ድጋፍ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ጋር ብቻ መሆኑም ተነግሯል። ሕዝብ ግንኙነቱ ግን አዲስ አበባ በሚገኘው ቢሮና ሰሜን አሜሪካ በሚገኘው ጽሕፈት ቤት በኩል ልዩነት እንዳለ የሚነሳው ስህተት መሆኑና በሁለቱም መሀከል ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ አለኝ ብለዋል፡፡

ከፓርቲው ሕልውና ጋር በተያያዘ የአቶ እስክንድር መልቀቅ ተከትሎ “ፓርቲና ግለሰብ ይለያያል፡፡ ግለሰቦች ይለዋወጣሉ፡፡ ፓርቲ ግን ተቋም ነው፤ አንድ ግለሰብ ሲወጣ የሚፈርስ አይደለም” ሲሉ ፓርቲው ይፈርሳል የሚለው ስጋት መሰረተ ቢስ መሆኑንም ዶ/ር በቃሉ አስረድተዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img