- መቐለ ደርሰው የተመለሱት የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ ለድርድሩ እንቅፋት ነው ስላሉት ጉዳይ ተናግረዋል
አምባ ዲጂታል፤ ቅዳሜ ሐምሌ 30፣ 2014 ― የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛው ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፤ በአዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ጋር ይደራደራል ብሎ ከሰየመው ቡድን አባላት ጋር እንደሚወያዩ ኅብረቱ አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት በድረ ገጹ እንዳስታወቀው ልዩ መልእክተኛው ለዚሁ ሥራ ሐሙስ ሐምሌ 28፣ 2014 አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ በቆይታቸው ከተደራዳሪ ቡድኑ በተጨማሪ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ይወያያሉ ተብሏል፡፡
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ፤ ከሁለት ቀናት በፊት በፌዴራል መንግስቱ እና በሕወሓት መካከል የሚካሄደውን ሽምግልና በተመለከተ ለኅብረቱ የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ገለጻ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ሌላ መረጃ በአፍሪካ ቀንድ የአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አኔት ዌበር በመንግሥት እና ሕወሃት መካከል ያለው ያለመተማመን የሰላም ድርድር ለመጀመር እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሳምንት ከሌሎች ጋር መቐለ ደርሰው የተመለሱት ዌበር፤ ይህን የተናገሩት ለጀርመን ድምጽ ነው፡፡
ዌበር ሁለቱም ወገኖች ድርድር ለማድረግ ጠንከር ያሉ መተማመኛዎችን ይፈልጋሉ ያሉ ሲሆን፣ መንግሥት መሠረታዊ አገልግሎቶችን ከጀመረ ወይም እንደሚጀምር ፍንጭ ከሰጠ፣ ሕወሃት ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን መረዳት ችለናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ መንግሥት መሠረታዊ አገልግሎቶችን በቅርቡ ይጀምራል ብለው እንደሚጠብቁ ዌበር አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ዌበር የተካተቱበትና የአሜሪካ እና የአውሮፓ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች እንዲሁም በኢትዮጵያ የካናዳ እና የጣሊያን አምባሳደሮችን የያዘው ልዑክ ወደ ትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ያቀናው ማክሰኞ ሐምሌ 26 ነበር፡፡
ምዕራባውያኑ ዲፕሎማቶች ወደ መቐለ ተጉዘው ከሕወሓት መሪዎች ጋር መነጋገራቸውን ተከትሎ ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ ግጭቱን በሰላም ለመቋጨት ‹‹ፖለቲካዊ ውይይት አስፈላጊ ነው›› ብለው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ምዕራባውያኑ በነዳጅ፣ በጥሬ ገንዘብ እና በማዳበሪያ ላይ ተጥሎ ያለው ክልከላ መነሳት አለበት ያሉ ሲሆን፤ በክልሉ ተቋርጠው የሚገኙ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሰው ለሚጠግኑ ባለሞያዎች ደኅንነት የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ከትግራይ ለፌደራል መንግሥት ይዘው ተመልሰዋል፡፡
መግለጫው ተከትሎ ምላሽ የሰጡት የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን፤ ምዕራባውያኑ ዲፕሎማቶች በመቐለ ቆይታቸው የፌደራሉ መንግሥት ደስተኛ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ አምባሳደሩ ልዩ መልዕክተኞቹ እና አምባሳደሮቹ ለሰላም ንግግር ጥረት ማድረግ ሲገባቸው በሌላ ወገን የተቀመጠ ቅድመ ሁኔታ ማሟላት ላይ ተጠምደዋል ብለዋል።
ተቋርጠው የሚገኙ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በተመለከተ የመንግሥት አቋም ግልጽ ነው ያሉት አምባሳደር ሬደዋን፤ አገልግሎት ማስጀመር የሚቻልባቸው ሁኔታ መፍጠር እና የሰላም ንግግር መጀመር ቀዳሚ መሆን አለበት ብለዋል።
ልዩ መልዕክተኞቹ እና አምባሳደሮቹ ከመቀለ ጉዟቸው በኋላ ባወጡት መግለጫ ‹‹አሁንም ያልተገደብ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የሚል ትርክት እንደቀጠለ ነው›› ያሉት ሬድዋን፤ በአሁን ላይ ወደ ክልሉ ያልተገደብ በረራ እና የጭነት ካሚዮኖች ጉዞ እየተደረገ ነው ብለዋል። የነዳጅ ጉዳይም ቢሆን መፍትሔ እንደተሰጠው እና በሁሉም አድናቆት የተቸረው ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።