Sunday, September 22, 2024
spot_img

ሕወሓት ከመንግሥት ጋር ለድርድር የሚቀመጠው በኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አማካይነት እንደሆነ ጌታቸው ረዳ ገለጹ

አምባ ዲጂታል፤ ማክሰኞ ሐምሌ 12፣ 2014 ― ያለፉትን ሃያ ወራት ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በጦርነት ውስጥ የቆየው ሕወሓት፤ ከመንግሥት ጋር ለድርድር የሚቀመጠው በኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አማካይነት እንደሆነ ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል፡፡

ይህንኑ ቃል አቀባዩ ጌታቸው ነግረውኛል ብሎ ያስነበበው የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው፡፡ የዜና ወኪሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያሉበትን ተደራዳሪ ቡድን ‹‹ወደ ናይሮቢ ለመላክ ዝግጁ እንደሚሆኑ ገልጸዋል ያለው ሕወሓት ተደራዳሪዎችን መሰየሙን ባመለከተበት ዘገባው ነው፡፡

የአቶ ጌታቸው ይህ ንግግር የመጣው ባለፈው ሳምንት መንግሥት የሰየመው ተደራዳሪ ቡድን በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ለሚደረገው የሰላም ንግግር ሥራ መጀመሩን ማስታወቁን ተከትሎ ነው፡፡

መንግሥት ይህን ቢልም ሕወሓት ከዚህ ቀደም ለሽምግልና አዲስ አበባ እና መቐለ ሲመላለሱ የቆዩት የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‹‹ቅርበት አላቸው›› ሲል ስጋቱን ገልጾ ነበር፡፡

አዣንስ ፍራንስ ፕረስ አሁን ይዞት በወጣው ዘገባ አቶ ጌታቸው ‹‹ሁሉንም የድርድር ሂደቶች ለአፍሪካ ኅብረት ማቅረቡ ለኛ እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ነገር ይሆንብናል›› ማለታቸውን አመልክቷል፡፡ ቃል አቀባዩ አያይዘውም ‹‹ንግግሩ በሰላም ጥረት ውስጥ ንቁ ተሣትፎ ያላቸውን ኬንያታን ማሳተፍ ይኖርበታል›› ብለዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ረዳ ይህን ማለታቸው በሁለቱ አካላት መካከል ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው የሰላም ንግግር እንቅፋት ስለመፍጠሩ የታወቀ ነገር የለም፡፡ መንግሥትም የሕወሓትን ቃል አቀባይ ንግግር ተከትሎ ያለው ነገር የለም፡፡

የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ከመንግሥት ጋር የሚደረገው ንግግር በኬንያው ፐሬዝዳንት በኩል ይሁን ከማለታቸው በተጨማሪ አወዛጋቢ ሆኖ የቆየውን የምዕራባዊ ትግራይ አካባቢ ለድርድር እንደማያቀርቡ ገልጸዋል፡፡

ሁለት ዓመት በተጠጋውና ባለፉት ወራት ጋብ ባለው የፌዴራል መንግስት እና ሕወሓት ጦርነት በርካታ ሺሕዎች መቀጠፋቸው ይታመናል፡፡ በተጨማሪም ሚሊዮኖች ከትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ተፈናቅለዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img