Sunday, November 24, 2024
spot_img

ሕወሓት የኦባሳንጆን አደራዳሪነት እንደማይፈልግ ገለጸ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ሰኔ 08 2014 ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ለአስራ ዘጠኝ ወራት ግጭት ውስጥ የቆየው ትግራይ ክልልን የሚመራው ሕወሓት የአፍሪካ ኅብረት የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑኩ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆን አደራዳሪነት እንደማይፈልግ የገለጸው ትላንት ማክሰኞ ግንቦት 7፣ 2014 በሊቀመንበሩ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በተጻፈ ደብዳቤው ነው፡፡

ደብረጽዮን ለአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ማኪ ሳል፣ ለኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ለተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሸይኽ መሐመድ ቢን ዛይድ እና ለታንዛንያው ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሐሰን ሱሁሉ በጻፉት ደብዳቤ በኦባሳንጆን ሽምግልና የገለልተኛነት ጥያቄ አንስተው፣ በአንጻሩ የኬንያው ፕሬዝዳንት አደራዳሪ እንዲሆኑ ፍላጎታችን ነው ብለዋል፡፡

በዋነኝነት ለአራቱ መሪዎች የተጻፈው ደብዳቤ፤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ፣ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊመንበር ሙሳ ማሕመት ፈቂ፣ ለተመድ የአሜሪካ ተወካይ ቶማስ ሊንዳ ግሪንዲልድ፣ ለአዲሱ አሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ፣ ለአውሮፓ ኅብረት እና ለኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ግልባጭ ተደርጓል፡፡

የሕወሓት ሊቀመንበር የኦባሳንጆን አደራዳሪነት ገሸሽ ለማድረጋቸው፤ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ቅርበት አላቸው የሚል ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሊቀመንበሩ ኦባሳንጆን የላኳቸውን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ማኪ ሳልን በክፉ ቀን ዝምታን መርጠዋል ሲሉ በብርቱ ተችተዋል። 

የዶክተር ደብረጽዮን ደብዳቤ የመጣው ቡድናቸው ከሰሞኑ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በሰኔ ወር መጨረሻ በታንዛን አሩሻ ድርድር ሊያደርግ ነው በሚል መነገሩን ተከትሎ ነው፡፡ የሕወሓት ሊቀመንበር በደብዳቤያቸው ስለ አሩሻው ድርድር ያሉት ነገር ባይኖርም፤ የታንዛንያው ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሐሰን ሱሁሉ በኢትዮጵያ ሠላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ዝግጁነት አሳይተዋል በሚል አድንቀዋል፡፡

በተመሳሳይ የትግራይ ክልል መንግሥት እንዲያደራድረን እንፈልጋለን ላሏቸው ኡሁሩ ኬንያታም ‹‹ገለልተኛ መሆናቸውን ያስመሰከሩና እምነት የምንጥልባቸው መሪ ናቸው›› በማለት አወድሷል፡፡ ደብዳቤው በዚሁ ሽምግልና አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በድርድሩ እንዲሳተፉ ፍላጎት እንዳለው ዘርዝሯል።

ይኸው ደብዳቤ አክሎም ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን በተመለከተ ‹‹ለሰላም ተጨማሪ ርቀት ለመሄድ ዝግጁ መሆናችን ከደካማነት ወይም ከስግብግብነት በመነጨ የቆምንለትን መርህ ለመተው እንደ መዘጋጀት ተደርጎ መታየት የለበትም›› ብሏል።

የፌዴራል መንግሥቱ ከዚህ የደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ደብዳቤ በኋላ ያለው ነገር ባይኖርም፣ ከደብዳቤው ሰዓታት ቀድመው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ እና ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ አሕመድ፤ የሚመሩት መንግሥት ከየትኛውም ወገን ጋር ሠላም ማውረድ እንደሚፈልግ በመግለጽ፤ ለዚህም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚቴው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ እንደሆነና በገዥው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ መሰየሙን ያመለከቱት ዐቢይ፤ ሠላሙን በተመለከተ መሳካት ያለባቸው ተግባራትን፣ እንዲሁም ስለሚጠበቁ ነገሮች እያጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕወሓት ጋር በሚደረገው ድርድርም እርሳቸው ሳይሆኑ ይኸው ኮሚቴ ተደራዳሪ መሆኑን እንዲሁም ኮሚቴው በቅርቡ የደረሰበትን ለፓርቲው ሲያቀርብ በይፋ ለሕዝብ በዝርዝር የሚቀርብ ይሆናል ብለዋል።

በፓርላማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ሆኑ ምሽቱን ደብዳቤ ለዓለም ያሠራጩት የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ድርድር እየተካሄደ መሆኑን በሚመለከት የወጡ ዘገባዎችን አስተባብለዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img