Sunday, November 24, 2024
spot_img

ሕወሓት ግንቦት 20 በሽራሮ በኩል ከኤርትራ ጦር ጥቃት ተሰንዝሮብኛል አለ

  • የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ቃል አቀባይ ተንኳሹ ሕወሓት ሊሆን ይችላል ብለዋል

አምባ ዲጂታል፤ ማክሰኞ ግንቦት 23 2014 ከፌዴራል መንግሥት ያለፉትን 19 ወራት ግጭት ውስጥ የሚገኘው ሕወሓት፤ በጦርነቱ ከፌዴራል መንግሥት ጎን የተዋጋው የጎረቤት አገር ኤርትራ ጦር ቅዳሜ ግንቦት 20 እና በማግሥቱ ግንቦት 21፣ 2014 በሽራሮ በኩል ጥቃት ተከፍቶብኛል ያለው በቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ በኩል ነው፡፡

አቶ ጌታቸው በትዊተር ባሠፈሩት ጽሑፍ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኤርትራ ተሰንዝሮብናል ካሉት ጥቃት በተጨማሪ ግንቦት 16 በተመሳሳይ ከአገሪቱ 57ኛ እና 21ኛ ክፍለ ጦር አዲአዋላ በተባለ ሥፍራ ወደ ትግራይ ክልል ጥቃት ተሰንዝሮ መክተነዋል ብለዋል፡፡ እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ ጥቃቱን ተከትሎ የትግራይ ክልል ኃይሎች መልሶ ማጥቃት ፈጽመው ከ300 በላይ ወታደሮች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን እንዲሁም በርካታ የጦር መሣሪያ መማረካቸውን አመልክተዋል፡፡

በአቶ ጌታቸው የተጠቀሰውን ጥቃት በተመለከተ የኤርትራ መንግሥት እስካሁን ድረስ ምላሽ ባይሰጥም፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር የሆኑት ዶክተር ለገሠ ቱሉ ግን “በኤርትራ በኩል ጦርነት ይከፈታል የሚል እምነት የለንም” እንዳሉት ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

ዶክተር ለገሠ ጨምረውም የሕወሓት ኃይሎች ለጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለዚህ እንዲያመቻቸው ምናልባት በኤርትራ ኃይሎች ላይ ትንኮሳ ፈጽመው ከአገሪቱ በኩል ምላሽ ተሰጥቷቸው ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ማስቀመጣቸውም በዘገባው ተመላክቷል፡፡

አቶ ጌታቸው በበኩላቸው የኤርትራ ኃይሎች “ቀጠናውን ወደማያባራ ግጭት እየወሰዱት ነው” ሲሉ በመክሰስ ይህ መሆኑ ‹‹ወደ ሰላም ሊደረግ የሚችል ጉዞን የሚያሰናክል›› ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ሚያዝያ መጨረሻ ላይ የትግራይ ኃይሎች ከኤርትራ ጋር አዋሳኝ በሆኑት አካባቢዎች ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከፍተው ለአጭር ጊዜ የቆየ ወታደራዊ ግጭት መካሄዱ ተዘግቦ ነበር፡፡ በወቅቱ ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለው በራማ እና ባድመ አካባቢ ባለው የኤርትራ ጦር ላይ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ጥቃቱን ተከትሎ በትግራይ ኃይሎችና በኤርትራ ጦር መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተገልጿል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኤርትራ ህወሓት ለዳግም ጦርነት በዝግጅት ላይ እንደሆነ በመግለጽ እራሷን ለመከላከል አስፈላጊውን ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን ገልጻ እንደነበርም ይታወሳል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img