አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ግንቦት 17፣ 2014 ― የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ቀድሞ በምክትል ሊቀመንበርነት አሁን ደግሞ በሥራ አስፈፃሚ ውስጥ የሕግና ሥነ ምግባር ጉዳዮች ኃላፊ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ዩሱፍ ኢብራሂም ፓርቲው ትላንት ባወጣው መግለጫ እጄ የለበትም ብለዋል።
አብን ትላንት ምሽት በፌስቡክ ለቆት ኋላሜ ባልተገለጸ ምክንያት ጠፍቶ በድጋሚ ተመልሶ አስተያየት መስጫው ዝግ በተደረገው መግለጫው፣ መንግሥት የፓርቲውን አመራሮችና አባላት ጨምሮ በአማራ ክልል እያካሄደው ያለውን ጅምላ እስር በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቋል። ፓርቲው ጨምሮም በፖለቲካ አቋማቸው የተነሳ የታሰሩ ግለሰቦች በአስቸኳይ እንዲለቀቁና ሕወሃት ለሌላ ዙር ጦርነት እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት በአማራ ክልል የሕዝባዊ አመጽ ጥሪ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
በሌላ በኩል በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ቡድኖችና ግለሰቦች እና በአማራ ብሄርተኝነት ሽፋን በማኅበራዊ ትስስር ዘዴዎች የሚደረጉ ቅስቀሳዎች ለክልሉ አለመረጋጋት ምክንያት መሆናቸውን ገልጿል።
ይህንኑ የፓርቲውን መግለጫ ተከትሎ የግል አቋምን ስለመግለፅ በሚል ርእስ ምላሽ የሰጡት የሥራ አስፈፃሚ አባሉ አቶ ዩሱፍ፣ ለጊዜው በድርጅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዝርዝር ሀሳቦችን የመሰንዘር ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለጽ፣ ሆኖም ከችግሩ ግዝፈትና አሳሳቢነት አንፃር መግለጫው ሊፈጥር የሚችለውን አንድምታና የሞራል ጫና በዝምታ ለመጋራት ፍቃደኛ መሆን አልችልም በማለት ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።
በዚህም ከመነሻው የተፈፀመውን ጥሰት ለመረዳትና ለመቃወም ይሄን ያክል ረጅም ጊዜ መቆየት አያስፈልግም የሚል እምነት አለኝ ያሉት አቶ ዩሱፍ፣ አሁንም ቢሆን የሚያስፈልገው ከህግ የበላይነት መርኅ ጋር በፅኑ የተፋታውን የአፈናና የእስራት ተግባር በልኩ በመቃወምና በዋናነት የታዩ ጥሰቶችን በማንሳትና ተቃውሞን በማስመዝገብ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ እንደሌለበት እንደሚገነዘቡና ከመቼት አንፃርም ቢሆን የድርጅቱ ድርሻ የሆነውንና ያልሆነውን ነገር በቅጡ ለይቶ እንዳላስቀመጠ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ድርጅቱ የህዝብ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል ያሉት ዩሱፍ፣ የአቋም መግለጫውም ለህዝብ ሲባል የተደረገና ለህዝብም በይፋ የቀረበ እንደሆነ ታሳቢ ስለሚደረግ፣ ፓርቲውም በየሂደቱ የሚማር ተቋም በመሆኑ የአስተያየት መስጫው ዝግ ሊሆን አይገባም ነበር ሲሉ ተቃውመዋል።
በተለያየ መልኩ ለረዥም ጊዜ ወዲያና ወዲህ ሲሰነዘሩ የቆዩ ጉዳዮችን ያሏቸውን አጀንዳዎች ማጣቀስ ትክክል አይደለም ያሉም ሲሆን፣ ወቅቱን የማይመጥን መሆኑን ጠቁመው ይባስ ብሎ በተዘዋዋሪ መንገድ ለተፈፀመው አፈና ድጋፍ እንደመስጠት ሊያስቆጥር የሚችል ነው ሲሉ አንስተዋል።
ስለሆነም ለመላው ህዝብ፣ ለአባላት፣ ለደጋፊዎች እና በተለይም በእስር ላይ ለሚገኙ የአብን አመራሮችና አባላት በሙሉ እንደግለሰብ በዚህ ውስጥ እንደሌለሁበት እወቁልኝ ብለዋል።
ከመግለጫው በኋላ ሊቀመንበሩ ዶክተር በለጠ ሞላም አስተያየት ሰንዝረዋል። ዶክተር በለጠ በአስተያየታቸው በአማራ ፖለቲካ ውስጥ በጣም ቀላሉ ነገር የማህበራዊ ሚዲያውን ምዕመን እየሸነገሉ ማስደሰት ነው ያሉ ሲሆን፣ ይህን ማድረግ እጅጉን ቀላል መሆኑንም ገልፀዋል።
አክለውም ይህን ስታደርግ ጀግና ነህ፣ እንከን የለሽ ነህ፣ ንጹህ ነህ፣ ተቆርቋሪ ነህ፣ አሻጋሪ ነህ ያሉት በለጠ፣ ከባዱና ፈታኙ ነገር የህዝብን ጥቅም እያሰሉ በገደል መሀልም ቢሆን ቀጭኗን መንገድ ጠብቆ ለመጓዝ ጸንቶ መገኘት መሆኑን አንስተዋል።
በማሳረጊያቸውም ከባዱን መንገድ መርጠናል ጸንተን እንቆማለን በውጤቱም ነገ ላይ አንገታችንን ቀና አድርገን እንጓዛለን ብለዋል።
ከአብን ጋር በተገናኘ ሌላ መረጃ፣ የቀድሞ የአብን ሊቀመንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ከፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት መልቀቃቸውን አሳውቀዋል።
የአብን አመራሩ የፓርቲው ሪፎርም ተጠናቆ ፓርቲው ተጠናክሮ መቆም ሲችል ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸውም እንደሚለቁ ገልፀዋል።
አቶ ደሳለኝ በፌስቡክ ገፃቸው እንዳስታወቁት “ለአጭር ጊዜ ብዬ የተመለስኩበት ጊዜ ስለተጠናቀቀ እንዲሁም ወደፊት ጊዜው ሲደርስ በምገልፃቸው ምክንያቶች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከአብን ስራ አስፈፃሚ አባልነቴ በፈቃዴ የለቀቅሁ ሲሆን፤ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ግን የአብን ሪፎርም በስኬት እስኪጠናቀቅ የምቀጥል ይሆናል” ብለዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የካቲት ወር ላይ ባደረገው ጊዜያዊ የአስፈፃሚ ሪፎርም አብን በቀጣይ 3 ወር ውስጥ የሚያካሂደው ሪፎርም ተከናውኖ አዳዲስ አመራሮች እስኪመረጡ ድረስ ከ2 እስከ 3 ወር ላልበለጠ ጊዜ ወደ ስራ አስፈፃሚነት እንዲመለሱ የአብን ማዕከላዊ ኮሚቴ ወስኖ እንደነበር ይታወሳል።
አቶ ደሳለኝ የአብን ሪፎርም በስኬት እስከሚጠናቀቅ ድረስ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንደሚቀጥሉ አስታውቀው አዳዲስ መሪዎች በኮሚቴው ውስጥ እድል እንዲያገኙ ለማድረግ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነትም በፈቃዳቸው እንደሚለቁ ገልፀዋል።
አቶ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) አብን በወርሃ ሰኔ 2010 ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2012 ድረስ በሊቀ መንበርነት አገልግለዋል።