Saturday, November 23, 2024
spot_img

ሱዳን በአቢዬ ግዛት ለሚመደቡ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ አባላት ቪዛ ማጓተቷን ተመድ አስታወቀ

አምባ ዲጂታል – እሑድ ሚያዝያ 24፣ 2013 ― የሱዳን መንግሥት ከደቡብ ሱዳን ጋር ለሚወዛገብበት ለአብዬ የድንበር ግዛት ለሚመደቡ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት ቪዛ ለመስጠት ዳተኝነት ማሳየቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አስታውቀዋል።

ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ የአቢዬ ግዛት የፀጥታና የሰላም ስምምነት አተገባበርን አስመልክቶ ሰሞኑን ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት እንደተናገሩት፣ ተመድና የአፍሪካ ኅብረት በጣምራ ባሳለፉት ውሳኔ፣ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሠራዊትና ሲቪል አባላት ግዳጃቸውን በጥሩ ሁኔታ እየፈጸሙ ነው።

በኢትዮጵያና በሱዳን መንግሥታት መካከል በተፈጠረው መጠነኛ አለመግባባት ምክንያት በአብዬ ግዛት የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲወጣ፣ በሱዳን መንግሥት በኩል ጥያቄ መቅረቡንም አመልክተዋል።

ይህ ጉዳይ ገና ውሳኔ ያለገኘ መሆኑን የተናገሩት ዋና ጸሐፊው፣ ጉዳዩ በአፍሪካ ኅብረት አመቻችነት የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳንና የኢትዮጵያ መንግሥታት እየመከሩበት እንደሆነም ገልጸዋል።

ተመድ እ.ኤ.አ. በ2019 ባሳለፈው ውሳኔ በአብዬ ግዛት የተሠማራው አጠቃላይ የሰላም አስከባሪ ኃይል ብዛት ወደ 3 ሺሕ 550 ዝቅ እንዲል፣ እንዲሁም የሰላም አስከባሪ ኃይሉ አካል የሆነው የፖሊስ ሠራዊት ቁጥር ከፍ እንዲል በወሰነው መሠረት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጥ አሠራሩ መሠረት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የጦር አባላትን ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን ይገልጻል።

ነገር ግን ከአንድ ወር በፊት ባለው መረጃ መሠረት የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላቱ ቁጥር በተመድ ከተወሰነው ከ3 ሺሕ 550 በታች መሆኑን የዋና ጸሐፊው ሪፖርት ያመለክታል።

በአሁኑ ወቅት ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከተቀመጠው ጣሪያ በታች 3,419 እንደሆነ የተናገሩት ዋና ጸሐፊው፣ በተመድ ከተቀመጠው የሰው ኃይል መጠን በ131 እንደሚያንስ ጠቁመዋል።

የሰላም አስከባሪው ሠራዊት አባላት ቁጥር ዝቅ ብሎ የፖሊስ አባላቱ ቁጥር 640 እንዲሆን ተመድ ከዓመት በፊት ቢወስንም፣ በአሁኑ ወቅት ያሉት የፖሊስ አባላት ብዛት 47 ብቻ መሆኑን በሪፖርቱ አመልክተዋል።

ለዚህም በዋና ምክንያትነት የጠቀሱት የሱዳን መንግሥት ቪዛ በመስጠት እየተባበረ አለመሆኑን ነው። ሪፖርቱ በሚሸፍነው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሱዳን መንግሥት ለቀረበለት የ163 አባላት የቪዛ ጥያቄ ምላሽ እንዳልሰጠ ዋና ጸሐፊው ያቀረቡት ሪፖርት ያመለክታል። ከተጠቀሰው ቁጥር ውስጥም 13 ለወታደራዊ አባላት፣ 77 ለፖሊስ አባላት የቀረበ የቪዛ ጥያቄ መሆኑም ተገልጿል።

ከአንድ ወር በፊ 11 ኦራል ተሽከርካሪዎች በአቢዬ ግዛት ለሚገኘው የሰላም አስከባሪ ኃይል የሎጂስቲክስ አቅርቦት ለማድረስ ከኢትዮጵያ ያደርጉት የነበረው ጉዞ በሱዳን የመከላከያ ኃይል ተገትቶ እንደነበር፣ ከአንድ ቀን በኋላም መፍትሔ ተገኝቶ ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉን ገልጸዋል።

በአቢዬ እንዲሰማራ የተወሰነው ሰላም አስከባሪ ኃይል ተልዕኮ በመጠናቀቅ ላይ ቢሆንም፣ በአካባቢው የሚፈለገው ሰላም ገና ባለመረጋገጡ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ ቆይታ ይራዘም ወይም አይራዘም በሚለው ላይ ተመድና የአፍሪካ ኅብረት ውሳኔ ማሳለፍ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።

ይህ ጉዳይ ገና ውሳኔ ባላገኘበት በዚህ ወቅት የሱዳን መንግሥት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል መውጣት አለበት የሚል አቋም መያዙን ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንዲሁም በጋራ ድንበር ላይ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው ቅራኔ፣ ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲወጣና ከተለያዩ አገሮች በሚውጣጣ ቅይጥ ኃይል ሊተካ ይገባል የሚል አቋም እንደያዘች ገልጸዋል።

የደቡብ ሱዳን መንግሥት ይህንን የሱዳን መንግሥት አቋም እንዳልደገፈ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ሁለቱም መንግሥታት የኢትዮጵያ ጦር እንዲወጣ የሚጠይቁ ከሆነ ለመውጣት ዝግጁ መሆኑን፣ ነገር ግን የአቢዬ ግዛት የሰላም ሁኔታ በሁለቱ አገሮች መካከል ቅራኔ ፈጥሮ ዳግም እንዳያገረሽና ይህም በሁለቱ አገሮች ብሎም በኢትዮጵያ ላይ የደኅንነት ቀውስ እንዳይፈጥር ሥጋት እንዳለው ገልጸዋል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የአፍሪካ ኅብረትና የተመድ ተወካዮች ከሦስቱ አገሮች አመራሮች ጋር ምክክር እያደረጉበት እንደሚገኝ የጠቀሱት ዋና ጸሐፊው፣ የአፍሪካ ኅብረት ጉዳዩን አስመልክቶ የያዘው አቋም ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት በአቢዬ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል የሚወጣበት ሁኔታ፣ የነዋሪዎችንና የቀጣናውን ደኅንነት አደጋ ላይ በማይጥል አግባብ ብቻ መፈጸም አለበት የሚል አቋም መያዙንና ይህም በእሳቸውም የሚደገፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአቢዬ የሚገኘው የሰላም አስከባሪ ኃይል የተወሰኑ አባላት መክዳታቸውን የተመለከቱ ዘገባዎች የተሰሙ ቢሆንም፣ በአቢዬ ያለውን የአንድ ዓመት ሁኔታ የተመለከተው የተመድ ዋና ጸሐፊ ሪፖርት ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው ነገር አለመኖሩን የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img