Thursday, November 21, 2024
spot_img

የኢሳት ቦርድ ከሥያሜ መብት ጋር በተገናኘ የቀድሞ ጋዜጠኞቹን በፍርድ ቤት ከሰሰ

አምባ ዲጂታል፤ ማክሰኞ መጋቢት 20 2014 ― የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ቦርድ ከሥያሜ መብት ጋር በተገናኘ የቀድሞ ጋዜጠኞቹን በፍርድ ቤት መክሰሱን አስታውቋል፡፡

መጋቢት 14፣ 2014 በውጭ አገር ሲሠሩ የቆዩ የኢሳት ጋዜጠኞች ከጣቢያው ተነጥለው የራሳቸውን ‹ኢሳት ኢንተርናሽናል› የሚል የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን መመሥረታቸውን ማሳወቃቸው አይዘነጋም፡፡

ሲሳይ አጌና፣ ፋሲል የኔዓለም፣ መሳይ መኮንን እና ሌሎችንም የያዘው ስብስብ፣ የራሱን መገናኛ ብዙኃን ለማቋቋሙ የኢሳት ቦርድ አለበት ያለውን ችግር ዘርዝሮ ነበር፡፡

ይህን ተከትሎ የኢሳት ቦርድ ባወጣው ሌላ ምላሽ ኢሳት ተከፈለ ብለው መናገራቸውን ትክክል አለመሆኑን ገልጾ፣ የተቋሙን ገንዘብ፣ ንብረቶችና የማይዳሰስ ያለውን ሐብት ጠብቆ ለማቆየት አለብኝ ያለውን ኃላፊነት ለመወጣትና ሥያሜውን ለማስከበር ሕጋዊ ርምጃ እወስዳለሁ ሲል አስጠንቅቆ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ በዛሬው እለት ባሠራጨው መግለጫ ቦርዱ በትላንትናው እለት መጋቢት 19፣ 2014 በቨርጂንያ ግዛት ፍርድ ቤት አቤቱታውን ማቅረቤን እወቁት ብሏል፡፡

የኢሳት ቦርድ ይህን ባሳወቀበት መግለጫው፣ ይህን ርምጃ ስንወስድ ‹‹የኢሳትን ሕልውና ለመከላከል ከሕግ ሌላ አማራጭ›› ስላጣሁ ነው ብሏል፡፡

ከኢሳት ቦርድ ክስ በኋላ ‹‹ኢሳት ኢንተርናሽናል›› በሚል አዲስ የመገናኛ ብዙኃን የመሠረቱት የቀድሞው የጣቢያው ጋዜጠኞች ይህ ዘገባ እስከተሰናዳበት ሰአት ድረስ የሰጡት ምላሽ የለም፡፡

ከዚሁ ከኢሳት ኢንተርናሽናል ጋር በተያያዘ ሌላ መረጃ፣ አዘጋጆቹ ከቀናት በፊት ከቀድሞ ጣቢያቸው መለየታቸውን በገለጹበት ወቅት ወደ ሳተላይት እስኪመለሱ ድረስ በሚኖረው ጊዜ ከዩትዩብ ሥርጭታቸው በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ መቀመጫውን ባደረገው ‹‹ባላገሩ›› የተሰኘ ቴሌቪዥን ጣቢያ በኩል እንደሚደርሱ ገልጸው ነበር፡፡

ነገር ግን ጋዜጠኞቹ በተለይ የሚታወቁበት ‹‹ዕለታዊ›› የተሰኘ ፕሮግራማቸውን በጣቢያው ከትላንት መጋቢት 19፣ 2014 አንስቶ ለማስተላለፍ ዝግጅቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን በተላለፈ ጥያቄ ፕሮግራሙ ሳይተላለፍ መቅረቱን አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት አዘጋጆቹ፣ ለተመልካቾቻቸው ውጤቱን የምናሳውቃችሁ ይሆናል ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የሰጠው ምላሽም ሆነ ማብራሪያ የለም፡፡

ከአስር ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው ኢሳት፣ ከዚህ ቀደም ሌሎች ባልደረቦቹም በተመሳሳይ ተነጥለው የራሳቸውን የበይነ መረብ ብዙኃን መገናኛ እንዳቋቋሙበት ይታወሳል፡፡  

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img