Friday, November 22, 2024
spot_img

የዩኬ ፓርላማ የአገሪቱ መንግሥት በትግራይ ያለውን ግጭት ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን መጠቀም አለበት አለ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 23፣ 2013 ― የዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ የትግራይ ክልልን በሚመለከት በትላንትናው እለት ባወጣው ሪፖርት የአገሪቱ መንግሥት በክልሉ ያለውን ግጭት ለማሰቆም በተቻለው ሁሉ የዲፕሎማሲ አማራጮችን መጠቀም እንዳለበት ገልጧል፡፡

ፓርላማው የዩኬ መንግሥት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የሚካሄደውን ግጭት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማስቆም ኃላፊነት እንዳለበትም ነው ጨምሮ የገለጸው፡፡

በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ቁልፍ ምክንያቱ በክልሉ ያለው ግጭት ነው ያለው ፓርላማው፣ በክልሉ እየተካሄደ ያለው ጦርነት የሰብዓዊ ርዳታ ለማቅረብ የሚደረውን ጥረት ማደናቀፉን አክሎ ገልጿል። ለዚህም የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ግጭቱ አንዲቆም በተቻለው መጠን ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን መጠቀም አለበት ሲል ድምዳሜ ሰጥቷል።

አክሎም ግጭት ለማስቆም የዩኬ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት፣ ከአፍሪካ ሕብረት፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ በግጭቱ ተሳታፊ ከሆኑ አካላት እና ከጎረቤት አገራት ጋር አብሮ መስራት አለበት ያለ ሲሆን፣ በግጭቱ በተለይ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የተቃጣው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እጅጉን እንዳሳዘነው በማመልከት ወንጀሉ ተመርምሮ ጥፋተኞች ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል ዜጎችን ከጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች መጠበቅ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊነት መሆኑን የብሪታኒያ መንግሥት የኢትዮጵያን መንግሥትን ማሳሰብ አለባት ሲል ፓርላማው ምክረ ሐሳቡን ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎቹን ደህንነት ለማረጋገጥ እርምጃ መውሰድ ቢሳነው፤ የዩኬ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታተ የጄኖሳይድ ኮንቬንሽንን መሠረት ባደረገ መልኩ ኃላፊነት የመውሰድ ግዴታ እንዳለበት ማወቅ አለበት ብሏል።

ይህ እንዲፈጸም የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በትግራይ ክልል የተፈፀሙ ወንጀሎች በአግባቡ ተመርምረው አጥፊዎቹ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንዲሰራ መጠየቁን የዘገበው ቢቢሲ ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img