Sunday, September 22, 2024
spot_img

ባልደራስ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ የብልጽግና አባል ይነሱ በሚል ያቀረበውን የድጋፍ ጥያቄ በምርጫ ቦርድ ውድቅ አደረገ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ የካቲት 14 2014 ― ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) የካቲት 7፣ 2014 ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት የብልጽግና አባል አቶ ዘላለም ሙላቱን ከምክር ቤት ለማስነሳት ድጋፍ እንዲደረግለት ያቀረበውን ቅሬታ ውድቅ ተደርጓል፡፡

ፓርቲው በእለቱ በጻፈው ደብዳቤ አቶ ዘላለም የካቲት 3፣ 2014 በአዲስ አበባ ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር ‹‹በኦሮሚያ ል ዞን ስር የሚገኙ አካባቢዎች አዲስ አበባ ከርሷን ሞልታ ፈርሷን የምትጥልባቸው ናቸው›› ማለታቸው በማስረጃ ስለተረጋገጠ፣ ከሕዝብ እንደራሴነታቸው የሚነሱበትንና የማሟያ ምርጫ የሚደረግበትን ሒደት ለማስጀመር ድጋፍ ይደረግልኝ ሲል ጠይቆ ነበር፡፡

ለዚሁ ጥያቄ ምርጫ ቦርድ በዛሬ እለት በሰጠው ምላሽ፣ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት መራጩ ሕዝብ አመኔታ በሚያጣበት ወቅት ተወካዩን ሊጠራ የሚችልበትን መብት ማረጋገጡን የገለጸ ሲሆን፣ አመኔታ ያጣው ተመራጭ ከመቀመጫው እንዲነሳ ሲደረግ ሕዝብ ውክልናውን መልሶ እንዲያገኝ የማሟያ ምርጫ እንደሚደረግ መደንገጉን አስታውሷል፡፡ ሆኖም ተመራጩ ይውረድልኝ የሚለው ሕዝብ መሆኑን ሕገ መንግስቱን ጠቅሶ አስገንዝቧል፡፡

በመሆኑም አግባብነት ባለው የሕግ ማዕቀፍ መሠረት በምርጫ ክልሉ ነዋሪ የሆነ መራጭ ሕዝብ ጥያቄውን ሲያቀርብ ቦርዱ መርምሮ ውሳኔ ከሚሰጥበትና በሰጠው ውሳኔ ላይ መሠረት በማድረግ ተወካዩ ተነስቶ የሟሟያ ምርጫ እንደሚያደርግ ያመለከተው ቦርዱ፣ ነገር ግን ከምክር ቤት መነሳትን በሚመለከት ለማንኛውም አካል በተለይም በምርጫ ክልሉ ተወዳዳሪ ለሆነ ፓርቲ ድጋፍ የሚያደርግበት የሕግ አግባብ ስለሌለ ባልደራስ ያቀረበውን ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡

ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ምላሽ ተከትሎ ምላሹን አፅንኦት በመስጠት እየተከታተለው መሆኑን ያስታወቀው ባልደራስ፣ በጉዳዩ ዙሪያ በቀጣይ ይፋዊ ምላሽ እሰጣለሁ ብሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img