Sunday, September 22, 2024
spot_img

የሶማሌ ክልል መንግሥት የተፈጠረውን ድርቅ ለፖለቲካ መጠቀሚያ የሚያደረጉትን አልታገስም አለ

(አምባ ዲጂታል) ሰኞ የካቲት 7 2014 ― የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት በኮሚኒኬሽን ቢሮ በኩል ባወጣው መግለጫ በአሁኑ ጊዜ በክልሉ የተፈጠረውን ድርቅ ለፖለቲካ መጠቀሚያ የሚያደረጉትን እንደማይታገስ አስታውቋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ድርቁን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ የክልሉ መንግስትና ሕዝብ ድርቁን ለመቀልበስ የሚያደርጉት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፣ ‹‹ፀረ ለውጥ›› ባላቸው ኃይሎችና ‹‹ለህዝብ ደንታ የሌላቸው ሴረኛ አካላት ለአፍታም›› አይሰናከልም ብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሶማሌ ክልል ህዝብ የተፈጥሮ የድርቅ አደጋ እንደገጠመው የገለጸው የክልሉ መንግሥት፣ ይህ ድርቅ በመላው የሶማሌ ክልል ህዝብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ማስከተሉን አመልክቷል፡፡

ይህ በዝናብ እጥረት ምክንያት ተከስቷል ያለውን ድርቅ ለመቋቋም ድርቁ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡

የክልሉ መንግሥት ትኩረቱን ሁሉ ‹‹ድርቁን ለመቀልበስ›› ማዋሉን የጠቀሰ ሲሆን፣ ከተለያዩ ‹‹ወንድም ክልሎች››፣ ግለሰቦችና ድርጅቶች የተገኙ እርዳታዎችም ለህዝቡ ማድረስ ችያለሁ ነው ያለው፡፡

ይሁን እንጂ ከድርቁ ስፋትና ርዝመት አኳያ ይህ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ለተለያዩ የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ጥሪ አቅርቦ ከተለያዩ የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ አካላት እርዳታ መገኘቱንም ገልጧል፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተደረጉ የሚገኙ ድጋፎችን የዘረዘረው የሶማሌ ክልል መንግስት፣ ሆኖም ይህን በሚደረግበት ጊዜ ሙስና የፈጸሙ እንዲሁም ‹‹ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር በነበራቸው ድብቅ ግንኙነት ከመዋቅር የወጡ›› ያላቸው ግለሰቦች በውጭና በሀገር ውስጥ ተሰባስበው ‹‹በሸረቡት ሴራ›› የክልሉንና የህዝባችንን ሰላም ለማወክ ሙከራ አድርገዋል ብሏል፡፡

የእነዚህ ኃይሎች ዋና አላማ ‹‹ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት፣ ክልሉን ለማተራመስና ስልጣንን በሀይል ለመያዝ ነው›› ያለው የሶማሊ ክልል መንግስት፣ ለህዝብ ደንታ የላቸውም ያላቸው እነኚህ ሀይሎች ‹‹ሰላም ለማደፍረስና በድርቅ የተጎዱ ዜጎች እየተደረገ ያለውን እርዳታ ለማሰናከል›› ያደረጉት ሙከራም መክሸፉን ነው የገለጸው፡፡

የሶማሌ ክልል መንግሥት አያይዞም ስልጣን በምርጫ እንጂ በሀይል ለመያዝ የሚደረግ ሙከራ ፈፅሞ የሚሳካ እንዳልሆነ የገለጸ ሲሆን፣ ድርቁን ለመቀልበስ የሚያደርገውን ስራ ለአፍታም በ‹‹ፀረ ለውጥ አካላት አይሰናከልም›› ብሏል፡፡

ጨምሮም ድርቁን ለመቀልበስ እያደረግኩ ካለሁት ርብርብ ውጭ ‹‹ክልሉን የጦር አውድማ ለማድረግና ሰላምን ለማወክ ሴራ እየሸረቡ ከሚገኙ አካላት እና በድጋሚ ወደ መንግሥት መዋቅር ለመመለስ በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር በመታገል›› ስለምገኝ ይህን በጋራ ለመመከት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

የክልሉ መንግስት በመግለጫው ማሳረጊያ ድርቁን ለመቀልበስ ከሁሉም ሰብአዊነት ከሚሰማቸው ዜጎች ጋር በጋራ እንደሚሠራ በመግለጽ፣ ሆኖም ለፖለቲካ አጀንዳቸው ብለው ድርቁን ለፖለቲካ መጠቀሚያ የሚያደረጉት ‹‹ሴረኞችን›› ግን አልታገስም ሲል አሳስቧል፡፡

 የሶማሌ ክልል የብልጽግና ፓርቲ የተወሰኑ አመራርና አባላት በክልሉ ገዢ ፓርቲ የሆነው ፓርቲያቸው ውስጥ ተንሰራፍቷል ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመታገል የእርምት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ባወጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር፡፡

የቡድኑን መግለጫውን በተመለከተ የተናገሩት የሶማሌ ብልጽግና ፓርቲ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሐመዴ ሻሌ ግለሰቦቹ ከዚህ ቀደም በለውጡ ሰሞን ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ የተባረሩ ናቸው ብለዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img