Wednesday, November 27, 2024
spot_img

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአካባቢው ካሉ ታጣቂዎች ጋር እየተነጋገረ መሆኑ ተገለጸ

  • ታጣቂዎቹ በክልሉ ውስጥ ድርሻ ይኑረን እና ከክልሉ ውጪ ያሉ የፀጥታ ኃይሎች እንዲወጡ የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው ተሰምቷል

አምባ ዲጂታል፣ረቡዕ የካቲት 2፣ 2014 ― በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው የካማሺ ዞን አስተዳደር በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች በኩል፣ በዞኑ ከሚገኙ ታጣቂዎች ጋር እየተነጋገረ መሆኑ ተገልጧል፡፡

በዞኑ አስተዳደርና በታጣቂዎች መካካል የሚደረገው ንግግር ‹‹ጥሩ ደረጃ›› ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ ታጣቂዎቹ ያሏቸውን ጥያቄዎች በሽማግሌዎች በኩል በደብዳቤ አቅርበው ሁለቱም አካላት በተነሱ አጀንዳዎች ላይ መስማማታቸው ነው የተነገረው፡፡

በቅርቡ አዳዲስ አመራሮች እንደ ተሾሙለት የተነገረው የካማሺ ዞን፣ አዲሶቹ አመራሮች ያዋቀሯቸው የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ወደ የሚገኙበት ያሶ ወረዳ ሄደው ታጣቂዎቹን ማነጋገራቸው ተገልጿል፡፡ ከዞኑ አስተደዳር የተላኩት እነዚህ ልዑካን ከታጣቂዎች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ በታጣቂዎቹ በኩል የተወከሉ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን ይዘው ወደ ካማሺ ከተማ መመለሳቸው ተሰምቷል፡፡

በሁለቱም በኩል ያሉ ልዑካን ጥር 21፣ 2014 ይዘው የመጡትን የውይይት ሪፖርት በተመለከተ፣ ከዞኑ አመራሮች እንዲሁም በዞኑ ከሚገኙና ከክልሉ የፀጥታ አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብጅጋ ጻፊዮ እንደነገሩት ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል፡፡ ከውይይቱ በኋላም በሁለቱም ወገን ያሉ ሽማግሌዎች ተመልሰው ወደ ታጣቂዎቹ ዘንድ መሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡

በካማሺ ከተማ በተደረገው ውይይት ላይ ታጣቂዎቹ ለሰላም ፍላጎት እንዳላቸው በሽማግሌዎቹ በኩል መግለጻቸውን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፣ ታጣቂዎቹም ሆነ የክልሉ መንግሥት ባሏቸው አጀንዳዎች ላይ መግባባት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ታጣቂዎቹ በመንግሥት በኩል ‹‹ኃላፊነት የሚወስድ አካል የግድ መኖር አለበት›› የሚል ሐሳብ በማንሳት፣ ይኼንኑ የሚገልጽ ሕጋዊ ደብዳቤ ተጽፎ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን አቶ ብጅጋ ተናግረዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደርም ልዑካኑ በድጋሚ ወደ ታጣቂዎቹ ሲመለሱ ይኼንኑ የሚገልጽ ደብዳቤ ይዘው እንዲመለሱ ማድረጉን አክለዋል፡፡

ጋዜጣው ያነጋገራቸው የካማሺ ዞን ኮማንድ ፖስት ዋና አስተባባሪ ኮሎኔል ዓለሙ በሽር እንዳስረዱት፣ ታጣቂዎቹ ካነሷቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ በእስር ላይ ያሉ አባሎቻቸው ይፈቱ የሚል ነው፡፡ የዞኑ አስተዳደሮች ይኼ ጥያቄ በዞኑ የሚመለስ እንዳልሆነ አስረድተው፣ በጉዳዩ ላይ ከበላይ አካላት ጋር ንግግር በማድረግ መልስ እንደሚሰጡ ማስታወቃቸውን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም በመተከል ዞን የሚገኙና ከክልሉ ውጪ ያሉ የፀጥታ ኃይሎች እንዲወጡ የሚል ጥያቄ መኖሩን ያስታወቁ ሲሆን፣ ይኼንን ጥያቄ በተመለከተም ኮሎኔል ዓለሙ፣ ‹‹የሌሎቹን አላውቅም፤ የፌዴራል ፖሊስና መከላከያ ሠራዊትን ግን ማስወጣት አይችሉም፣ ይኼ አይመለስላቸውም እርግጠኛ ነኝ›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ‹‹በክልሉ ውስጥ ድርሻ ይኑረን›› የሚል ጥያቄ እንደተነሳ ጠቁመዋል፡፡

የካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብጅጋ በበኩላቸው ታጣቂዎቹ በልዑካኑ በኩል ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ በዞን ደረጃ የሚስተናገዱትን እንደሚመለሱ፣ በክልል ወይም በፌዴራል ደረጃ የሚመለሰውን ደግሞ የዞኑ አስተዳደር ለበላይ አካላት እንደሚያስታውቅ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መስተዳደር 2013 ላይ ከታጣቂዎች ጋር የሰላም ስምምነት ተፈራርሞ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በጊዜው ታጣቂዎቹ ያላቸውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የፖለቲካ ጥያቄ አቅርበው ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጾ ነበር፡፡ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰንና በታጣቂዎቹ ተወካይ አማካይነት፣ በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ላይ በተፈረመው ስምምነት አማካይነትም ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና ሲሰጣቸው ነበር፡፡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥም በጀት ተይዞ ሥራ ተጀምሮ እንደነበር፣ እንዲሁም በመንግሥት መዋቅር ውስጥም የማሳተፍ ዕርምጃ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ይሁንና በክልሉ መንግሥት ‹‹ከሕወሓት ጋር አብረው ይሠራሉ›› የሚል ወቀሳ የሚነሳባቸው ታጣቂዎቹ፣ ከሰኔ 2013 ጀምሮ፣ የሕወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች መስፋፋት ሲጀምሩ ታጣቂዎቹ ስምምነታቸውን አፍርሰው ወደ ጫካ መግባታቸው ተነግሯል፡፡

አሁን በካማሺ ዞን የተደረገው ዓይነት ልዑካንን ወደ ታጣቂዎች የመላክ ሥራ በመተከል ዞንም ተሞክሮ እንደነበር ለሪፖርተር ያስረዱት የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ፣ የተላኩት የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ድብደባና እንግልት እንደ ደረሰባቸው አስታውሰዋል፡፡

ኃላፊው፣ አሁን ባለው ሁኔታ ታጣቂዎቹ ትጥቅ እንደሚፈቱ፣ እንዲሁም ሰላማዊ ሁኔታን እንደሚፈልጉ ማስታወቃቸውን ገልጸው፣ ‹‹ትጥቅ መፈታት አለበት፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ወደ ማኅበረሰቡ ይቀላቀሉ፣ ሌሎች ጉዳዮች በቀጣይ የሚታይ ነው የሚሆነው፣ ጥያቄም ካለ በውይይት የሚፈቱ ነገሮች ይኖራሉ›› ብለዋል፡፡

የካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብጅጋ በበኩላቸው፣ ‹‹ሽማግሌዎቹን ስንልካቸው በሰላም ነው ደርሰው የተመለሱት፣ ስለዚህ ነገሩ በሰላማዊ መንገድ እንደሚያልቅ ነው ተስፋ ያለን›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img