Thursday, November 21, 2024
spot_img

የአ/አ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ1 ሚሊዮን 45 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በካርታ ማስተላለፉን አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ረቡዕ የካቲት 2 2014 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ1 ሚሊዮን 45 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በካርታ ማስተላለፉን ያስታወቀው፣ ለሲኖዶሱ በመስቀል አደባባይ ጉዳይ ቶሎ ተገናኝተን እንነጋገር ባለበትና ጥር 30 በተጻፈ ደብዳቤው ነው፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተፈረመውና በጽሕፈት በኩል በወጣው ደብዳቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ‹‹የለውጥ ዓመታት›› ባለው ጊዜ አዳዲስ ውሳኔዎችን በመወሰን የቤተ ክርስትያንዋን ጥያቄ እየመለስኩ ነበር ብሏል፡፡

ለአብነት ያክል ብሎ በጠቀሰው የ1 ሚሊዮን 45 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት በካርታ የማስተላለፍ ውሳኔ የ89 ቦታዎች መሆኑን ገልጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አራት ኪሎ የሚገኘውንና በደርግ ዘመን ተወርሶ ነበር ያለውን ‹‹መንትያ ሕንጻ›› በመመለስ የከተማ አስተዳደሩ ለቤተክርስትያን ያለውን አጋርነት ሲያረጋግጥ መቆየቱንም አመልክቷል፡፡

የከንቲባ አዳነች አቤቤ ደብዳቤ የመጣው ከሰሞኑ ከሲኖዶሱ ጋር ሊካሄድ የነበረ ውይይት ሳይሳካ መቅረቱን ተከትሎ ነው፡፡

እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሆነ ጥር 25፣ 2014 ከሲኖዶሱ ጋር ተገናኝቶ ውይይት ለማካሄድ ስምምነት ተደርሶ፣ የከተማ አስተዳደሩ ሰዎች በቀጠሮ ቦታ እና በሰአቱ ቢገኙም ሲኖዶሱ ተለዋጭ ቀጠሮ ስለጠየቀ ውይይቱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

የከተማ አስተዳሩ ለውይይቱ አለመሳካት የሲኖዶሱን በቦታው አለመገኘት ቢያነሳም፣ ከሲኖዶስ በኩል ይፋዊ ማብራሪያ አልተሰጠበትም፡፡

ኋላም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባለፈው እሑድ ጥር 29 ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋር መገናኘታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በዚሁ ደብዳቤ ከአቡነ ማትስ ጋር ‹‹ችግሩን በውይይት ፈጥነን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ተወያይተናል›› ብለዋል፡፡

ሆኖም ‹‹በተለያዩ የማኅበራዊ ድረ ገጾች በከተማ አስተዳደሩ የተያዘ ፕሮግራም ያለ በማስመሰል አስተዳደሩ የማያውቀው የተሳሳተ መረጃ ለሕዝብ እየተሠራጨ›› መሆኑን የጠቀሰው ደብዳቤው፣ ‹‹ይህንኑ ሕዝቡን የማደናገርና የማሳሳት ተግባር ለማስቆምና ፈጥነን ችግሩን በውይይት መፍታት ይቻል ዘንድ›› ለዛሬ የካቲት 2 ሲኖዶሱ ተወካዮቹን ወደ ከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እንዲልክ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ በበኩሉ ትላንት የካቲት 1 በጻፈው ደብዳቤ ‹‹ጥር 1፣ 2014 በመስቀል አደባባይ የተከናወነው ሑነት›› የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያንን ‹‹እጅግ ያስቆጣ ድርጊት›› መሆኑን በመጥቀስ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ዐርብ የካቲት 4 በመንበር ፓትርያርኩ እንዲገኙ ሲል ለከንቲባ አዳነች አቤቤ ደብዳቤ ጽፏል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥር 30፣ 2014 ስለተጻፈው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ ያለው ነገር የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img