አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥር 27፣ 2014 ― የአፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመላ ሀገሪቱ ጥሎት የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጪው ሳምንት እንዲሚያነሳው አምባ ዲጂታል ከታመኑ ምንጮቹ ሰምቷል፡፡
ጥር 18፣ 2014 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ በሚመለከት በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል፡፡
‹‹ሕወሓት እና ግብረ አበሮቹ›› በአገሪቱ ህልውና እና ሉአላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ›› ጥለዋል በሚል መነሻ ሐሳብ ተጥሎ የቆየው አዋጁ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈፃሚነት ጊዜ ማሳጠር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የሚኒስትሮች ም/ቤት መግለጹ ይታወሳል።
ይህንኑ ተከትሎ የሚነሳው የአስቸኳይ ጊዜ በቀጣይ ሳምንት ሲነሳ፣ ከአዋጁ ጋር በተገናኘ የታሰሩ በርካታ ግለሰቦችም እንደሚለቀቁ ነው ምንጮች ለአምባ ዲጂታል የጠቆሙት፡፡
ይህንኑ በተመለከተ የአምባ ዲጂታል ምንጮች የአዋጁን መነሳት ተከትሎ ከእስር የማይለቀቁ ግለሰቦች ክስ እንደሚመሰረትባቸው ነው የተናገሩት፡፡
በኢትዮጵያ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገው ጥቅምት 23፣ 2014 ሲሆን፣ አዋጁ የመጣው ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ወደ አዲስ አበባ በመቶ ኪሎ ሜትሮች በተቃረበበት ወቅት ነበር።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ከቀናት በፊት መግለጫ ያወጣው ኢሰመኮ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያበቃ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ውሳኔው አበረታች እርምጃ ነው ሲል አድናቆቱን ገልጿል።
ኢሰመኮ በመግለጫው አያይዞም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳ መሆኑን ከሚያጸድቅበት ቀን ጀምሮ ከእስር ያልተለቀቁ ሰዎች የሚኖሩ ከሆነ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለባቸው አሳስቧል።
ይህ ካልሆነ ግን እስሩ ከሕግ ውጭ ስለሚሆን የሁሉም የሕግ አስከባሪ አካላት የሕግ ማስከበሩን ተግባራት የሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ በመደበኛው ሥርዓት እንዲያከናወኑ ጠይቋል።