Sunday, September 22, 2024
spot_img

ኬንያ በቀጣይ አምስት ወራት ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥ ልትጀምር መሆኑ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥር 16፣ 2014 ― ጎረቤት አገር ኬንያ በቀጣይ ወራት ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥ ልትጀምር መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ኬን ግዥውን የምትጀምረው የኢትዮጵያና ኬንያ ኃይል ማስተላለፊያ ግንባታ መገባደድን ተከትሎ ሲሆን፣ አገሪቱ የመጀመሪያውን ግዥ በቀጣዮቹ ወራት ታከናውናለች ተብሏል፡፡

ከዓመታት በፊት በኬንያ እና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ በኢትዮጵያ በኩል እስከ ሁለቱ ሀገሮች ድንበር ድረስ የተከናወነው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታ ባለፈው ዓመት ተጠናቋል።

በኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መካከል በተደረሰው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት መሠረት ኬንያ በሚቀጥሉት አምስት ወራት ውስጥ ቅድመ ዝግጅቶቿን አጠናቃ የኤሌክትሪክ ግዥ ትጀምራለች ተብሎ ይጠበቃል።

የኃይል መስመር ዝርጋታው በኢትዮጵያ በኩል ከተጠናቀቀ ዓመት ቢያልፈውም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጩ እስካሁን ድረስ ያልተጀመረው በኬንያ በኩል ዝግጅቶች ስላልተጠናቀቁ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ሞገስ መኮንን ነግረውኛል ብሎ ዋዜማ ራድዮ ዘግቧል፡፡

የኤሌክትሪክ ሽያጩ ሲጀመር፣ ኢትዮጵያ ለኬንያ ከ1 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ ኃይል ትሸጣለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው ገልጸዋል።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ይህን የሁለቱን ሀገሮች ጉርብትና የበለጠ የሚያጎለብት ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ በሁለቱ ሀገራት በኩል ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው፣ በቀጣዮቹ ወራት የኤሌክትሪክ ሽያጭ ለመጀመር በኬንያ በኩል ያሉ ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ከ10 ዓመት በፊት የተጀመረው ይህ ፕሮጀችት አጠቃላይ ወጪው 1.3 ቢሊየን ዶላር ሲሆን፣ ከዓለም ባንክ $684 ሚሊየን ዶላር፣ ከአፍሪቃ ልማት ባንክ 338 ሚሊየን ዶላር ድጋፍና በሁለቱ ሀገራት (ኬንያ 88 ሚሊየን ዶላር ኢትዮጵያ 32 ሚሊየን ዶላር) ወጪ የሚሸፈን ነው።

የኀይል ማስተላለፊያ መስመሩ 1,068 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን በኢትዮጵያ 437 ኪሎ ሜትር በኬንያ ደግሞ 631 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img