Sunday, September 22, 2024
spot_img

ዶ/ር ደብረጽዮን በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ ኤርትራን ከጉዳዩ ማውጣት ይገባል አሉ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥር 13 2014 ― የሕወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ ኤርትራን ከጉዳዩ ማውጣት ይገባል ብለዋል፡፡

ዶክተር ደብረጽዮን ይህን ያሉት ዘ አፍሪካ ሪፖርት ላይ ባስነበቡት አስተያየታቸው ነው፡፡

በዚሁ ጽሑፋቸው በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ ከጉዳዩ መውጣት አለባት ያሏት ኤርትራ፣ በአሁኑ ጊዜ የሰሜን ምዕራብ እና ምሥራቃዊ ትግራይ አካባቢዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ይዛለች ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቷ ኢሳይያስ አፈወርቂም ትግራይን መበቀል ይፈልጋሉ ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፣ ለዚህ ምክንያት አድርገው ያስቀመጡት ኢሳይያስ በምሥራቅ አፍሪካ እና ከዚያ ያለፈ የፖለቲካ እና የወታደራዊ የበላይነቱን ኅልማቸው እንዲያበቃ ሕወሓት የመሪነት ሚናውን ወስዷል በሚል እምነት መነሻነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡  

ኢሳይያስ በውጊያ ሜዳ ለደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈትም በትግራይ ወታደራዊ እና የደኅንነት ሰዎች ላይ ቂም ቋጥረዋል ያሉ ሲሆን፣ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት የትግራይ ሕዝብ በማዋለድ እና በመጠበቅ ጉልህ ሚና ተጫውቶበታል ያሉትን የኢትዮጵያን የሕብረ ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዐት የማፍረስ ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በአሁኑ ጊዜ ኢሳይያስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ‹‹የአማራ ተስፋፊ›› ካሉት ልሒቅ ጋር ኅብረት እንዳላቸው በማንሳት፣ ይህ ኅብረት በሁለት አላማ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከነዚህ አላማዎች መካል የመጀመሪያው ወታደራዊ ድጋፍ በመስጠት ሕወሓት እና ትግራይን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ማግለል እና በመጨረሻም ማስወገድ ነው ብለዋል፡፡

አያይዘውም ኢሳይያስ ፀረ ሕወሓት ካሏቸው ቡድኖች ጋር የሚያደርጉትን ኅብረት የሚመለከቱት ኤርትራን የቀጣናው ሃያል ለማድረግ ኅልም መሰናክል የሚሆነውን ኃይል እንደማስወገድ ነው ሲሉም አስፍረዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መነገድ መፍታት የሚቻለው ኢሳይያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ተሳትፏቸውን የሚቀንሱ ጠንካራ እርምጃዎችን ከተወሰዱ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img