Sunday, October 6, 2024
spot_img

የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ የእርዳታ እህል መዝረፋቸው ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሚያዝያ 21፣ 2013 ― ✅ በቅርቡ የኢትየጵያን መሬት ለቀው ይወጣሉ ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተነገረላቸው የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል የእርዳታ እህል መዝረፋቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አግኝቼዋለሁ ያለውን የመንግሥት ዶክመንት ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡

እንደ ዘገባው ከሆነ ወታደሮቹ ወደ ትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲደርስ በሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎች የሚሠራጩ እህሎችን ነው መዝረፋቸው የተነገረው፡፡ ይኸው ክስተት ባለፈው ሳምንት ዐርብ ሚያዝያ 15 ማጋጠሙንም የዜና ወኪሉ ከእርዳታ ሠራተኞች ሠምቻለሁ ብሏል፡፡

በተጨማሪም ወታደሮቹ አንዳንድ የትግራይ ቦታዎች ላይ እርዳታው እንዳይደርስ ሲከለክሉ ነበር የተባለ ሲሆን፣ በዚሁ ምክንያት የተራድኦ ሠራተኞች ሲያለቅሱ መስተዋሉም ተነግሯል፡፡

ይህንኑ ጉዳይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የኮማንድ ፖስት ኃላፊ ኮማንደር ገብረመስቀል ተስፋማርያም አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ባለፉት ሁለት ሳምንታት አንዳንድ ቦታዎችን ለመድረስ ችግር ገጥሞናል›› ያሉት ኃላፊው፣ እነዚህ ቦታዎች በተለይ በኤርትራ ወታደሮች የተያዙ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ከኤርትራ የጦር አዛዦች ጋር ለመነጋገር ባልደረባቸውን መላካቸውን የሚናገሩት ኮማንደር ገብረመስቀል፣ ምላሹን እየተጠባበቅን ነው ብለዋል፡፡

የዜና ወኪሉ ስለ ጉዳዩ የጠየቅኳቸው የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ውንጀላውን አስተባብለዋል ሲል ገልጧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img