Sunday, October 6, 2024
spot_img

ነእፓ መንግሥት ከጦርነቱ አስቀድሞ በቁጥጥር ስር አውሏቸው የነበሩ ፖለቲከኞችን መፍታቱን በአዎንታዊ መልኩ እንደተመለከተው ገለጸ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥር 2 2014 ነጻነት እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) መንግሥት ከጦርነቱ አስቀድሞ በቁጥጥር ስር አውሏቸው የነበሩ ፖለቲከኞችን መፍታቱን በአዎንታዊ መልኩ እንደተመለከተው ባወጣው መግለጫው አስታውቋል፡፡

ባለፈው ዐርብ ታኅሣሥ 29፣ 2014 መንግስት በእስር ላይ የነበሩትን የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ አመራሮቹ አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባን እንዲሁም የባልደራስ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎችንም መፍታቱ ይታወሳል፡፡

መንግስት ከእነ ጀዋር መሐመድ እና እስክንድር ነጋ በተጨማሪ የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የታሰሩትን አንጋፋውን አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ 6 የሕወሓት አባላት መፍታቱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ነእፓ ስለ ግለሰቦቹ መፈታት በመግለጫው ያለው ነገር የለም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግስታቸው ‹‹ኢትዮጵያን አንድ አድርገን ለማፅናት ካለን ፍላጎት አንፃር›› ያደረገው ነው ያሉትን ይህን ውሳኔ ሦስት ፓርቲዎች ማለትም ኢዜማ፣ አብን እና እናት ፓርቲዎች ተቃውመውታል፡፡

በሌላ በኩል ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ በመግለጫው ‹‹በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ውድመት›› አድርሷል ያለውን የትግራይ ጦርነት መንግስት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰደውን እርምጃ ‹‹ወቅታዊ እና ተገቢ ነው›› ብሎ እንደሚያምን ገልጧል፡፡

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በኢትዮጵያ ‹‹እውነተኛ ሰላም እና መረጋጋትን ለማረጋገጥ›› ቀላሉ እና አዋጭ የሆነው መንገድ በልዩነቶች ዙሪያ ‹‹ጥልቅ ውይይት ማድረግ›› እንደሆነ በጽኑ እንደሚያምንም አስታውቋል፡፡

መንግስት ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት የወሰደው እርምጃ በጦርነቱ ምክንያት ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ እየከፈሉ ነው ያለውን ‹‹ከፍተኛ ዋጋ›› ከማስቆም እና በአገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋትን ለመፍጠር ካለው ፋይዳ ባሻገር፣ ሊካሄድ ለታሰበው ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁሟል፡፡

ፓርቲው አያይዞም መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊያሳይ በሚችል መልኩ ሌሎች አስፈላጊ የፖለቲካ እና የህግ ማሻሻያዎችን ሊያደርግ ይገባል ያለ ሲሆን፣ ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት ወደ ጦርነት ሲገባም ሆነ ጦርነትን ለማቆም የሚወስናቸው ውሳኔዎች ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እንዲሁም የሀገርን እና የህዝቦቿን ዘላቂ ጥቅም የሚያስከብሩ ሊሆን እንደሚገባውም ነው ያመለከተው፡፡

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በመግለጫው ማሳረጊያ ‹‹ጦርነቱ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም እንዲሁም ሁሉን አቀፍ እና እውነተኛ ብሄራዊ ምክክር እንዲካሄድ›› ሳደርገው የቆየሁትን ጥረት አጠናክሬ እቀጥላሁ ብሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img