Sunday, September 22, 2024
spot_img

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ባለፈው ዓመት የአገራቸው ጦር ትግራይ የገባው ሕወሓት በተኮሰው ሚሳኤል ተገፍቶ ነው አሉ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥር 2፣ 2014 ― የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የአገራቸው ጦር ባለፈው ዓመት ትግራይ የገባው ሕወሓት በተኮሰው ሚሳኤል ተገፍተን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ይህን የተናገሩት ለአገራቸው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ዘለግ ያለ ቃለ ምልልስ ነው፡፡

በወቅቱ ሕወሓት በኤርትራ ውስጥ ከ100 በላይ ቦታዎች ላይ ኢላማ ለማድረግ ማቀዱን የሚያሳይ ማስረጃ አለን ያሉት ኢሳይያስ፣ ጀብዱ ያሉትን በሕወሓት ተሰንዝሯል ያሉት ጥቃት ‹‹በተሳሳተ ስሌት›› የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ በኅዳር 2013 የመጀመሪያ ሳምንት ከ5 ሺሕ በላይ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች የኤርትራን ድንበር አቋርጠዋል ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ዓመት በትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ከተማ ለወራት የቆየው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰኔ ወር ላይ ‹‹ከመቀሌ ይወጣል ብለን አልጠበቅንም›› ሲሉ የተደመጡ ሲሆን፣ በወቅቱ የውጭ አካላት የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ እንዲወጣ ግፊት ያደርጉ እንደነበር አስታውሰው፣ ‹‹ያልጠበቅነውና ድንገተኛ›› ያሉትን የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ‹‹ስልታዊ ማፈግፈግ›› እንደነበርም ነው የተናገሩት፡፡

በሌላ በኩል የሕወሓት ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ከተሞች ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች ያደረጉትን ግስጋሴ፣ ያለ ሎጅስቲክስ የተደረገ መሆኑን በመጥቀስ፣ ‹‹ማንኛውም ጤነኛ ወታደራዊ አመራር›› የማይደፍረው ነው ሲሉ ተችተውታል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በቆይታቸው ባለፉት በርካታ ዓመታት ስላለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የገመገሙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው መቃቃር መቼ እልባት እንደሚያገኝ ማን እንደሚፈታው ትልቅ ጥያቄ ነው ብለዋል። አያይዘውም ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት ሳይመጣና ለዚህ የሚያበቃ ሥርዓተ መንግሥት ሳይዘረጋ ከመጣው ሥርዓት ሁሉ እየተፋተግን መቀጠል አንችልም። ለዚህም የራሳችንን አስተዋፅኦ ማበርከት ስላለብን እጃችንን አጣጥፈን የምንመለከተው አይሆንም፣ በዘፈቀደ ሳይሆን በእውቀትና በእቅድና በዲዛይን የሚደረግ ይሆናል›› በማለት አስረድተዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ስለ ኢትዮጵያ የተለያዩ ጉዳዮችን በዳሰሱበት ቃለ ምልልስ፣ ሕወሓት የኢትዮጵያን የተረቀቀውን ሕገ መንግሥት ከማንም በፊት እንዳነብ ሰጥቶኝ ነበር ያሉ ሲሆን፣ አደገኛ እንደነበር በመግለጽ ቅሬታቸውን መናገራቸውን አስታውሰዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ችግሮች ጋር በተገናኘ የምትከተለውን የብሄር ፌደራሊዝም አደገኛ ‹‹የፖሊሲ አደጋ›› ነው ብለውታል፡፡  

በትግራዩ ጦርነት የተሳተፈው የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አገር ኤርትራ ጦር፣ በቆይታው ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግና የስደተኛ ሕግ ጥሰቶችን ፈፅሟል በሚል በርካታ ክሶች ቀርበውበታል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ የአሜሪካ መንግሥት በአራት የኤርትራ ተቋማትና በሁለት ኤርትራውያን ላይ በተያዘው ዓመት ማዕቀብ መጣሉ አይዘነጋም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img