Sunday, October 6, 2024
spot_img

ኢዜማን ጨምሮ ሦስት ፓርቲዎች መንግሥት እነ አቶ ስብሐት ነጋን ከእስር መልቀቁን ተቃወሙ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥር 2፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍተሕ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና እናት ፓርቲ መንግሥት እነ ስብሐት ነጋን ከእስር መልቀቁን ተቃውመው በተናጠል መግለጫ አውጥተዋል፡፡

ከፓርቲዎች መካከል ኢዜማ እነ ስብሐት ነጋ ከእስር የተለቀቁት ‹‹በእነሱ አነሳሽነት የተቀጠፉ ሕይወቶች ቁስል ባልሻረበት እና የወደሙ አካባቢዎች እስካሁን ባላገገሙበት ሁኔታ› መሆኑን በመጥቀስ፣ ‹‹ተበዳይ ፍትህ ሳያገኝ እንዲሁም ሳይካስ በዳይን ነፃ ማውጣት በፍትህ ስርዓቱ መቀለድ፣ የሕዝባችንን ጉዳትም ማቃለል ነው›› ብሏል፡፡

ፓርቲው ጨምሮም ‹‹በጥድፊያ የሚደረጉ ውሳኔዎች ፍትህን በመጨፍለቅ በተቋማቱ ላይ ያለንን እምነት በሂደት የሚሸረሽሩ ናቸው›› ያለ ሲሆን፣ ‹‹ከሕዝብ ጋር ምክክር የጎደለው›› እንደሆነ እና ‹‹ግብታዊ›› ሲል የጠራውን እርምጃ፣ ‹‹የሀገር ባለቤትነት እና መብትን ለአመፀኛው፣ የፈለገው ነገር እስካልተፈፀመ ድረስ ሀገር ብትጠፋ ከቁብ ለማይቆጥረው እና የሕዝቧ ስቃይ ግድ ለማይሰጠው ኃይል አሳልፎ›› የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ ውሳኔውን የተቃወመው አብን፣ መንግስት እነ ስብሐት ነጋን መልቀቁን ‹‹የሀገርና የህዝብን ጥቅምና ክብር በፅኑ የሚጎዳ ታላቅ ታሪካዊ ስህተት›› ብሎታል፡፡

አክሎም ‹‹ግብታዊና ኢፍትሃዊ›› ሲል የጠራውን ውሳኔ፣ ‹‹በመንግሥት ህጋዊና ሞራላዊ መሰረት ላይ እየጎሉ የመጡትን ክፍተቶች የሚያረጋግጥ፣ በመንግሥትና በህዝብ መካከል በየጊዜው እየጨመረ የመጣው ርቀትና ያለመተማመን የሚያጎላ መሆኑን›› ገልጧል፡፡ ልክ እንደ ኢዜማ ሁሉ አብን ውሳኔው ‹‹አመፅንና አመፀኞችን የሚሸልምና ሰላማዊና ህጋዊ ፖለቲካን ክፉኛ የሚጎዳ›› እንደሆነ ነው ያስታወቀው፡፡

ሌላኛው ውሳኔውን በመቃወም መግለጫ ያወጣው ፓርቲ እናት በበኩሉ፣ በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብም ይሁን ድርጅት ህጋዊ ሂደት ሳይጠብቅ ‹‹ክስ ማቋረጥ›› ማሰናበት በሕግ ተቋማት ሥራ ላይ ያለውን ጣልቃ ገብነት ከማሳየቱም ባሻገር የፈላጭ ቆራጭነት ማሳያ ነው ብሎታል፡፡

መንግስት ለውሳኔው የሰጠውን ‹‹በእድሜ የገፉ ስለሆነ›› የሚል ምክንያት ደግሞ ‹ሀገር ለሕልውና እያደረገች ያለውን ጦርነት ዓላማ የሳተ፣ የሕግ አሠራር ሂደትን የጣሰ፣ በግለሰቦችና ገዢው ፓርቲ ፍላጎት ብቻ ዜጎች የሚታሠሩበት እና የሚፈቱበት መሆኑን ማሳያ ነው› ብሎታል።

ባለፈው ዐርብ ታኅሣሥ 29፣ 2014 መንግስት በእስር ላይ የነበሩትን አቶ ጀዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ እስክንድር ነጋን መፍታቱ ይታወሳል፡፡ ከነዚህ ፖለቲከኞች በተጨማሪ አንጋፋውን አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ የሕወሓት አባላት መፈታታቸው በተለይ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ በውሳኔው ላይ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ውሳኔው ‹‹ኢትዮጵያን አንድ አድርገን ለማፅናት ካለን ፍላጎት አንፃር›› የተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img