Sunday, November 24, 2024
spot_img

ጠ/ሚ ዐቢይ ክስ የተቋረጠለት ሰው በአግባቡ መጠቀም ካልቻለ ተመልሶ ሊታሰር ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥር 2 2014 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ክስ የተቋረጠለት ሰው በአግባቡ መጠቀም ካልቻለ ተመልሶ ሊታሰር ይችላል ሲሉ አስጠነቅቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት በትላንትናው እለት አዲሱ የመከለከያ ጠቅላይ መምሪያ ሕንጻ ምረቃ ሥነ ሥርዐት እና በአውደ ውጊያ ውሎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ለተባሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሜዳሊያ ሽልማት በተበረከተበት መድረክ ነው፡፡


በመድረኩ ላይ ባሰሙት ንግግር ‹‹የተሸነፉ›› ያሏቸው ኃይሎች ክስ እንዲቋረጥ እና ከእስር ቤት እንዲወጡ መደረጉን አስታውሰው፣ ይህ ሲደረግ ‹‹ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ይህ ቁጣ የተቀሰቀሰው በሁለት ቡድኖች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አንደኛው ቡድን ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ጭር ሲል የማይወድ፣ ሁል ጊዜ እያጋጨ በሰበር ዜና ብር የሚሰበስብ፣ የት እንዳለ የማይታወቅ፤ ካለበት ሆኖ ስንዋጋ ጦርነት አቁሙ የሚል፤ ስናቆም ተዋጉ የሚል አጓጉል ብልጣብልጥነት የሚያጠቃው እና እምብዛም ጆሯችንን የማንገልጥለት ቡድን ነው›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለተኛውን ቡድን ‹‹በዜናው ድንገተኝነት የደናገጠ፣ በነበረው ተጋድሎ እና ሁኔታ ጊዜውን፣ ገንዘቡን፣ ህይወቱን ለመስጠት የወሰነ ከያለበት ሀገር እና ክልል ተሞ ከሀገር እና ከህዝብ ጋር የዘመተ›› እኩይ ጠላት ሲሉ የጠሩትን ሕወሓት ‹‹አምርሮ የሚጠላና ከዚህ ጠላት ጋር የሚደረግ ማንኛውም ንግግር ኢትዮጵያን ይጎዳል ብሎ የሚያምን ቅን ተቆጪ ነው፤ የዚህን ቅን ተቆጪ ኃይል መንግስት ሙሉ በሙሉ ይረዳል ያደምጣል ለማስገንዘብም ጥረት ያደርጋል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ጉዳይ ያዘኑ፣ የተቆጡ የኢትዮጵያ ቁርጥ ቀን ልጆች ሲሉ ለጠሯቸው ‹‹የወሰድነው መድሃኒት ማስታገሻ አይደለም የወሰድነው መድሃኒት ፈዋሽ በመሆኑ የጎንዮሽ ጉዳት አለው፤ ይጎረብጣል ያማል›› ሲሉ ያስገነዘቡ ሲሆን፣ መድሃኒቱን ‹‹ለማዳን ብቻ ሳይሆን በጎንም የመጎርበጥ ባህሪ አለው። ለጊዜው የሚያስታግስ ሳይሆን ለልጆቻችንም የድልና የአሸናፊነት መንፈስ የሚያላብስ ስለሆነ እንደኛ ደጋግማችሁ ስታስቡት ጠቀሜታው ጎልቶ ይታያችኃል እናም ደግማችሁ ለማሰብ ልባችሁና አእምሯችሁ እንዲከፈት ዋናው አላማ የምትወዷትን ሀገር ኢትዮጵያን አንድ አድርገን ለማፅናት ካለን ፍላጎት አንፃር ብቻ የመነጨ መሆኑን እንድትገነዘቡ ቢያንስ ቢያንስ ጉቦ በልተን እንዳለቀቅናቸው እንድታስቡ ላሳስባችሁ እፈልጋለሁ›› ብለዋል፡፡

አያይዘውም ክስ የተቋረጠላቸውን ወገኖች ‹‹ስላሸነፍን መበቀል እየቻልን ይቅር ማለትን ስለመረጥን ክስ አቋርጠን እናተን ሳይሆን ከእናተ ጀርባ ያለውን ህዝብ አክብረን የወሰን መሆናችንን አውቃችሁ ይህን እድል ሳታበላሹ እንድትጠቀሙበት›› ሲሉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

ጨምረውም ‹‹ክስ ማቋረጥ ማለት ምህርት መስጠት ማለት አይደለም፤ ክስ የተቋረጠለት ሰው በአግባቡ መጠቀም ካልቻለ መልሶ የክስ መዝገቡን መምዘዝ›› የሚቻል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዐርብ ታኅሣሥ 29፣ 2014 መንግስት በእስር ላይ የነበሩትን አቶ ጀዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ እስክንድር ነጋን መፍታቱ ይታወሳል፡፡ ከነዚህ ፖለቲከኞች በተጨማሪ አንጋፋውን አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ የሕወሓት አባላት መፈታታቸው በተለይ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ቁጣ ቀስቅሷል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መዝገብ ክስ ከቀረበባቸው ውስጥ እነ ስብሐት ነጋ ከእስር የተለቀቁት ‹‹የጤና እና የዕድሜ ሁኔታን›› ከግምት በማስገባት መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img