Sunday, September 22, 2024
spot_img

በመንግሥት ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ደቡብ አፍሪካዊ አክቲቪስት መጤ ጠል ነው መባሌ አካውንቴን ጠልፈው የፈጠሩት መሰረተ ቢስ ወሬ ነው አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ታኅሣሥ 28 2014 ― በመንግስት ጥሪ ባለፈው ሰኞ ታኅሣሥ 25 ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ደቡብ አፍሪካዊ አክቲቪስት ሎንታታ ላክስ መጤ ጠል ነው መባሌ አካውንቴን ጠልፈው የፈጠሩት መሰረተ ቢስ ወሬ ነው ብሏል፡፡

አክቲቪስቱ ይህን ያለው ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረገው ቆይታ ወቅት ነው፡፡

የዜና አገልግሎቱ ኑሯቸውን ደቡብ አፍሪካ በማድረግ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ኢትዮጵያዊያንም ስለ ደቡብ አፍሪካዊው ሎንታታ ላክስ ‹‹የሚናፈሰው ወሬ የልጁን ለእውነት ዘብ መቆም ያላማከለ መሰረተ ቢስ መሆኑን›› አረጋግጠዋል ሲል አስነብቧል፡፡

አክሎም ደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ሌሎች አፍሪካዊያን ሃብትና ንብረት ላይ የሚደርስን ውድመትና ጥፋት በመፋለም ከለላ እያደረገላቸው እንደሚገኝም ምስክርነታቸውን ገልጸዋል ነው ያለው፡፡

ሎንታታ ‹‹ምቹ ቢሮ ውስጥ በመቀመጥ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሃሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት ኢትዮጵያን ከመደገፍ ሊያስቆሙኝ አይችሉም›› ማለቱም ነው የተመላከተው፡፡

ሰኞ እለት አዲስ አበባ የገባው አክቲቪስቱ ሎንታታ ላክስ፣ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት ባሉ ቀናት ለፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ባስተላለፈው የቪድዮ መልእክት እና ኢትዮጵያ ከደረሰ በኋላም ‹አፍሪካውያን ከሀገራችን ደቡብ አፍሪካ ለቀው ይውጡልን› የሚል ይዘት ሲያስተላልፍ የቆየ ነው፡፡

ሉንታታ ባለፈው ሳምንት ታኅሣሥ 22፣ 2014 በግል የዩትዩብ ገጹ ባሰራጨው ቪድዮ ‹‹2022 ደቡብ አፍሪካን የምናስመልስበት ዓመት ነው›› የሚል ርእስ በሰጠው ንግግሩ፣ ሕገ ወጥ ባላቸውና በተለያዩ ነገሮች ዝርፊያ እና ወንጀል ተሰማርተዋል ላላቸው የውጭ አገራት ዜጎች ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ይደመጣል፡፡

አክቲቪስቱ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ባሰራጨው ሌላ ቪድዮ ደግሞ እርሱ የፓርላማ ፕሬዝዳንት ነኝ በሚልበት የሱዌቶ ግዛት የውጭ አገራት ዜጎች በተለምዶ ‹‹ስፓዛ›› የሚባሉ ሱቆችን መክፈት እንደማይችሉ በማስጠንቀቁ መጤ ጠልነትን የሚያነሳሳ እና ጥላቻን የሚዘራ ነው በሚል መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡

ግለሰቡ ማክሰኞ ታኅሣሥ 26 በጻፈው የኢንስታግራም መልእክት አፍሪካውያንን ‹ወደ ሀገራችሁ ተመለሱ› የሚል ያሰፈረ ሲሆን፣ ወደ ደቡብ አፍሪካ ይደረጋል ያለውን ‹‹ሕገ ወጥ›› ስደት ‹‹የኒዮ ኮሎኒያሊስቶች ሴራ ነው›› ሲል ገልጾታል፡፡ ባለፈው ሳምንት ታኅሣሥ 22፣ 2014 ባሰፈረው የትዊተር ማስታወሻ ላይ ህገ ወጥ ለሚላቸው ስደተኞች ደቡብ አፍሪካን ለቀው እንዲወጡ ‹‹የመጨረሻ›› ማሳሰብያ ጽፏል፡፡

የሎንታታ ላክስ አገር ደቡብ አፍሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያን በስደት ተጠግተው የሚኖሩባት መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን፣ በቅርብ ዓመታት በተደጋጋሚ በደቡብ አፍሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎች አፍሪካውያን ላይ ጥቃት ሲደርስ ሎንታታ ላክስ እና ሌሎች ግብረ አበሮቹ ተባባሪ እንደነበሩ ይነገራል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img