አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ታኅሣሥ 26፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ከአጎዋ መውጣት የሀገሪቱ ኢኮኖሚያ ላይ ከባድ ጉዳት እንደሚያስከትል የገለጹት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በአሜሪካ መንግሥት ከ20 ዓመታት በፊት የተሰጣት ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የሚያደርገውን ‹‹አፍሪካን ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት›› (አጎዋ) ባለፈው ቅዳሜ ታኅሣሥ 23፣ 2013 ከጀመረው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት አንስቶ ማጣቷ ይታወቃል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከካፒታል ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ከዚህ ከታሪፍ እና ኮታ ነጻ የሚያደርግ እድል መውጣቷ በኢኮኖሚው ላይ ጉዳት እንደሚኖረው ጠቅሰው፣ ለማሳያነት በፈረንጆቹ ከ2016 ጀምሮ ቀድሞ 13 በመቶ የነበረው አጎዋን ተጠቅሞ የሚደረገው ኤክስፖርት ኋላ ላይ ቁጥሩ ወደ 70 በመቶ ደርሶ ነበር ብለዋል፡፡
አያይዘውም በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚገኙ 35 ዋንኛ ኩባንያዎች መካከል በተለይ በአልባሳት እና ጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የሚገኙት የምርታቸውን 80 በመቶ አጎዋን ተጠቅመው ወደ አሜሪካ ገበያ ይልኩ እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፣ በአሜሪካ መንግስት የተላለፈው ውሳኔ በነዚህ ኩባንያዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ መንግስት እነዚህ ኩባንያዎች በገበያው ተፎካካሪ ሆነው እንዲቆዩ አማራጮችን እየፈለገ ነው መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፣ ከነዚህ አማራጮች መካከል የሕግ፣ መዋቅራዊ እና የሥርዐት ማሻሻያዎችን እንዲሁም ድጎማም አንስተዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚክስ ቡድኑ በዚሁ ላይ እየሠራ ይገኛል ያሉት አቶ ሳንዶካን፣ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በቅርቡ የሚተላለፉ ውሳኔዎች እንደሚኖሩም ጠቁመዋል፡፡
አጎዋ በአሁኑ ጊዜ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ቀጥረው የሚያሠሩ የውጭ አገር ባለሐብቶችና አልሚዎች፣ ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ትልቁ ምክንያታቸው እንደነበር ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በ2012 ብቻ በዚህ የነፃ ገበያ ዕድል ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመቱ ምርቶች ወደ አሜሪካ መላኳን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡