Saturday, September 21, 2024
spot_img

በውጭ ባንኮች ያልተወራረደ ሒሳብ ያለባቸው ባንኮች ዕዳቸውን እስኪከፍሉ ኤልሲ እንዳይከፍቱ ተወሰነ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሚያዝያ 20፣ 2013 ― ከውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምና ብድር አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በውጭ ባንኮች ያልተወራረደ ሒሳብ ያለባቸው ባንኮች ዕዳቸውን እስኪያወራርዱ ድረስ ተጨማሪ ሌተር ኦፍ ክሬዲት (ኤልሲ) እንዳይከፍቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ መጻፉ ተሰምቷል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ይህን የወሰነው ባንኮች ሌተር ኦፍ ክሬዲት በመክፈት የሚፈቅዱትን የውጭ ምንዛሬ ብድር በአግባቡ ውጭ ላለው ባንክ መክፈልና አለመክፈላቸውን ለማረጋገጥ ባደረገው ፍተሻ ወደ ሰባት የሚደርሱ ባንኮች ከፍተኛ ያላወራረዱት ሒሳብ እንዳለባቸው በማረጋገጡ ነው ተብሏል፡፡

እነዚህ ባንኮች ኤልሲ ከፍተው የፈቀዱትን የውጭ ምንዛሪ ከኢትዮጵያ ውጭ ላለው ባንክ መክፈልና ሒሳባቸውን ማወራረድ ሲገባቸው፣ ይህን ሒሳብ ሊከፍሉ በሚችሉበት ወቅት ባለመክፈላቸው እየቀረበ ባለ አቤቱታ መሠረት ብሔራዊ ባንክ ወደ ዕርምጃ ሊገባ እንደቻለም ባንኩ በጻፈው ደብዳቤ ተጠቅሷል፡፡

ይህንኑ ጉዳይ በሚመለከተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት አንድ ባንክ ሌተር ኦፍ ክሬዲት ከከፈተ በኋላ ሒሳቡን በውጭ በሚገኘው ባንክ ለደንበኛው የፈቀደውን ያህል የውጭ ምንዛሪ መክፈል ይኖርበታል ተብሎ የተቀመጠው በሦስት ወር ውስጥ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ባንኮች ግን ለዓመታት ያላወራረዱት ሒሳብ እንዳለባቸው ተሰምቷል፡፡

ባንኮቹ በውጭ ባንክ በኩል ማወራረድ የነበረባቸውን ገንዘብ ባለማወራረዳቸው እየፈጠረ ያለውን ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሰሞኑን የተወሰደው ዕርምጃ አስተዳደራዊ ቅጣትንም ያካተተ ስለመሆኑ ሪፖርተር ሰምቻለሁ ብሎ ዘግቧል፡፡

ይህ ደብዳቤ የደረሳቸው ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ጋር የመከሩበት ሲሆን፣ በመመርያው የተቀመጠውን አስተዳደራዊ ቅጣት ተቀጥተው ኤልሲ አትክፈቱ የሚለው የብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ግን እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡ ትዕዛዙ ከተተገበረ ባንኮች አደጋ ላይ የሚወድቁ በመሆኑ ይህ ታሳቢ መደረግ እንዳለበት አቤት ያሉ ሲሆን፣ አቤቱታቸው እስካሁን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ መልስ አላገኘም፡፡

ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀረበ አቤቱታ መሠረት ደቡብ ግሎባል ባንክ እንዲህ ያለውን ሒሳብ ባለመክፈሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የደቡብ ግሎባልን የ2012 የትርፍ ክፍፍል እንዳይፈጸም ማገዱን ዘገባው አስታውሷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img