ጎረቤት ሱዳን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ዐብደላ ሐምዶክን ጨምሮ በ15 የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ጋዜጠኞች ላይ እስከ ሞት ሊያስቀጣ የሚችል ክስ የመሠረተችው ትላንት ረቡዕ መጋቢት 25፣ 2016 ነው። የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን እንደዘገበው፤ በአሁኑ ሰዓት ሁለቱ ጀነራሎች ማለትም ዐብዱልፈታህ አል ቡርሃን እና መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመሩትን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት እሠራለሁ የሚለው ‹‹ተቀዱም›› የተሰኘውን የፖለቲካ ኃይሎች ጥምረት የሚመሩት ዐብደላ ሐምዶክ ላይ የተመሠረተው ክስ አገራቸው ላይ ጦር የመስበቅ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱን የመናድ እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀልን ያካትታል። ክሱ ዓብደላ ሐምዶክ ብቻ ሳይሆን በእርሳቸው ዘመን ባለሥልጣናት የነበሩትን መርየም አል ሳዲቅንና የፓርቲ መሪዎችን እንዲሁም ጋዜጠኞች የተካተቱበት ነው። አሁን እየተካሄደ ከሚገኘው ጦርነት ጋር በተገናኘ የተመሠረተው ክስ በሱዳን ሕግ ሞት ሊያስቀጣ የሚችል ነው፡፡
በሐምዶክና ሌሎችም የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ክሱን የመሠረተው የሕግ አካል የሚተዳደረው ሱዳንን ከፖርት ሱዳን እያስተዳደረ በሚገኘው በዐብዱልፈታህ አል ቡርሃን በሚመራው የሉአላዊ ሽግግር ምክር ቤት ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ሥልጣናቸው የተፈነቀለውም በዐብዱልፈታህ አል ቡርሃንና ጦርነት በገጠሟቸው ዳጋሎ ነበር፡፡ በርግጥ አል ቡርሃን እና ዳጋሎ ሐምዶክን አልነበረም ከሥልጣን የፈነቀሉት፤ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ዑመር አል በሽርንም ጭምር ነው፡፡ ሐምዶክ ከሥልጣን በተባረሩበት ወቅት ታስረዋል የሚሉ መረጃዎች ቢወጡም የመፈንቅለ መንግሥት መሪው አል ቡርሃን ግን ‹አታስቡ እኔ ቤት ነው ያለው› ሲሉላቸው የነበሩ ናቸው፡፡ ከሥልጣን የተባረሩት የዚያን ጊዜው የሲቪል መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ፤ ሁለቱ ጀነራሎች እርሳቸውን አባረው ሥልጣን አልበረክት ብሏቸው ወደ እርስ በእርስ ፍልሚያ ሲገቡ ተመልሰው የመጡት ‹‹በአሸማጋይነት›› ሚና ነው፡፡ ሐምዶክ ጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲበጅለት ይሠራል ያሉትን የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ጥምረት መርተው አዲስ አበባ ላይ ውይይት ሲያካሄዱ አሜሪካ፣ ዩኬ እና ኖርዌይ በገንዘብ ደግፈዋቸዋል፡፡
እነ አሜሪካ በሱዳን ሰላም ለማስፈን የሚያግዝ ነው ያሉት የሐምዶክ ጥምረት በጦርነቱ ተፋላሚዎች እኩል ይሁንታ የነበረው አይደለም፡፡ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪው ዳጋሎ ከጥምረቱ ጋር ለመሥራት ሲስማሙ፤ የአል ቡርሃን ወገን ሐምዶክ የሚመሩት ጥምረት የዳጋሎ አፈቀላጤ ነው በሚል ትችት ሲያቀርብበት ሰንብቷል፡፡ በዚህ ብቻ ሳያቆም የአል ቡርሀን ደጋፊዎች በቅርብ ጊዜያት በእነ ሐምዶክ ላይ ክስ እንዲከፈት ሲቀሰቅሱ ተስተውለዋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የመጣው ክስ በቀጣይ ጦርነቱ እንዲቆም እሠራለሁ በሚለው ‹‹ተቀዱም›› እና አገሪቱን በሚመሩት የጦር ጀነራል መካከል ቀድሞም የነበረውን ክፍተት በማጥበብ የንግግር እድሎችን የሚዘጋ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡ [አምባ ዲጂታል]