- “የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋዜጠኞች የማይጥማቸው ነገር በተናገሩ ቁጥር ከማሰር መቆጠብ አለባቸው” የሲፒጄ ኃላፊ
አምባ ዲጂታል፤ ሐሙስ መጋቢት 5፣ 2016 – ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (ሲፒጄ) የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ያለ ምንም ቅድመ ኹኔታና በስቸኳይ ጋዜጠኛ ሙሂዲን መሐመድ አብዱላሂን ከእስር እንዲለቁ የጠየቀው ባወጣው መግለጫ ነው።
በሲፒጄ እንዲፈታ የተጠየቀለት ሙሂዲን ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ውስጥ ተቀምጦ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘገባዎችን የሚሠራ ጋዜጠኛ ነው። ጋዜጠኛው የታሠረው የካቲት 5፣ 2016 እንደሆነ ሲፒጄ በመግለጫው አስታውቋል።
እንደ ሲፒጄ ከሆነ የሶማሌ ክልል ፖሊስ፣ ሙሂዲንን ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት ክስ የመሠረተበት ሲሆን፣ ጥፋተኛ ሆኖ የሚገኝ ከሆነ እስከ አምስት ዓመት እስር ይጠብቀዋል።
ሲፒጄ ባለሥልጣናት በጋዜጠኛው ላይ የመሠረቱትን ክስ እንዲያነሱና ትችት የሚሰነዝሩ ጋዜጠኞችን ከማሠር እንዲቆጠቡ ጠይቋል።
የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ሙቶኪ ሙሞ “የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋዜጠኞች የማይጥማቸው ነገር በተናገሩ ቁጥር ከማሰር መቆጠብ አለባቸው” ብለዋል።