Thursday, November 21, 2024
spot_img

ኢትዮጵያ እና ሱማሊያ በባለሥልጣናት በኩል የተካረሩ ቃላት ከመወራወር ለመቆጠብ መስማማታቸው ተሰማ

አምባ ዲጂታል፤ ሰኞ የካቲት 25፣ 2016 – በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የባህር በር ስምምነት ተከትሎ በመሃላቸው ውጥረት የሰፈነው ኢትዮጵያ እና ሱማሊያ በባለሥልጣናት በኩል የተካረሩ ቃላት ከመወራወር ለመቆጠብ መስማማታቸው ተሰምቷል፡፡

የሁለቱ አገራት መሪዎች ወደዚህ ስምምነት የደረሱት ባለፈው ሳምንት ከኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር በመጋረጃ ጀርባ በተናጠል ከተወያዩ በኋላ መሆኑን ዘ ኢት አፍሪካን የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ሁለቱ አገራት ከተጀመረው አዲስ ሳምንት አንስቶ የተካረሩ የቃላት ልውውጦችን ያለዝባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተነገረ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ጉዳዩን በአደባባይ ከማራገብ ለመቆጠብ መስማማታቸውንም የድረ ገጹ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በኢትዮጵያ እና ሱማሊያ መካከል ከመጋረጃ ጀርባ ከስምምነት ተደርሶበታል የተባለው ይህ አጀንዳ የመጣው ኬንያ ባለፈው ሳምንት ወደ አገሯ ለይፋ የሥራ ጉብኝት የተጓዙትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ናይሮቢ የገቡትን የሱማሊያውን ፕሬዝዳንት ሐሰን ሸይኽ ማሕሙድን ካስተናገደች በኋላ ነው፡፡

እንደ ዘገባው ከሆነ በጉዳዩ ዙሪያ በቅርቡ ከሁለቱ አገራት መሪዎች ጋር ለመወያየት ያቀዱት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከዚህ ቀደም ለማነጋገር ሙከራ ቢያደርጉም የሱማሊያው ሐሰን ሸይኽ ማሕሙድ እምቢታ በማሳየታቸው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ሆኖም ሩቶ በቅርብ ቀናት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ሁለቱ አገራት የአገራትን ሉአላዊነት ለማክበር ተስማምተናል ማለታቸው ሱማሊያን እንዳስተሰተ ተነግሯል፡፡ ሩቶ በአንጻሩ ኢትዮጵያ የኬንያውን ላሙ ወደብ እንድትጠቀም አስማምተው ሁለት ጉዳይ አሳክተዋል ነው የተባለው፡፡

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ጃንዋሪ 1፣ 2024 በአዲስ አበባ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ የሶማሊያ መንግሥት ካቢኔ ለአስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት ሶማሊላንድ የፌደራል መንግሥቱ አንድ አካል መሆኗን አስረግጧል። ስምምነቱንም ‹‹በሶማሊያ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ የተቃጣ ጥቃት ነው›› ብሎታል። በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ስምምነቱ ማንንም ለመጉዳት የተደረገ እንዳልሆነ ሲያስረዱ ታይተዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img