ጉዳዩ ትላንት ፌብርዋሪ 1፣ 2024 አንድ ወር ሞላው። በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመርያ ቀን አመሻሽ ላይ “ሰበር ዜና” ተብሎ በብሔራዊ ቴሌቪዥን የተላለፈው ዜና አየሩን የተቆጣጠረው በፍጥነት ነበር። ብሔራዊ ጣቢያውን ጨምሮ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጎላ ተገርጎ የቀረበው ዜና ኢትዮጵያ “ወደብ አገኘች” የሚል ነበር።
ዜናው ከመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ጎን ለጎን በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የመንግሥትን አጀንጃ በማስተጋባት በሚታወቁ የግለሰብ አካውንቶችም የጮኸ ነበር።
ይህ ዜና በሰዓቱ በመንግሥት መገናኛ ሲቀርብ ዝርዝሩ አልተነገረም። ኢትዮጵያ ወደብ አግኝታበታለች የተባለበትን ስምምነት ከሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር የተፈራረሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ናቸው። በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዜናው ይፋ ሲደረግ በኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) “ፈጣሪ ይመስገን እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል!” አስብሏቸዋል።
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ዜናው በዚህ መንገድ እንዲጎላ ሲደረግ፣ የጉዳዩ ተግባራዊነት ላይ እንዲሁም ዝርዝር ጉዳዮችን አንስተው “በጥሬ ሐቆች” ላይ መጠነኛ ጥርጣሬያቸውን የገለጹ ተስተውለዋል። እንደ ልደቱ አያሌው ዓይነት ፖለቲከኞች ወደቡን “የጨረቃ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመችው የሶማሊላንድ ሰዎች ደግሞ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ሙሉ ደስታቸውን የሚገልጽ ነበር። ሰዎቹን ያስደሰተው በፕሬዝዳንቱ ሙሴ ቢሂ በሱማሊኛ የተነገረው ጉዳይ ነው። በፊርማ ሥነ ሥርዐቱ ከኢትዮጵያው ዐቢይ ጎን የተቀመጡት ሙሴ፣ ለኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ ሲያከራዩ ኢትዮጵያ በምትኩ የአገርነት እውቅና ትሰጠናለች አሉ።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር ሶማሊላንዶችን ሲያስፈነድቅ፣ በአንጻሩ አሁንም ድረስ ሶማሊላንድን የግዛቴ አካል ናት የምትለው ሱማሊያን አስቆጣ። የተቆጡት ሱማሊያውያን ጉዳዩን ከሉዓላዊነት ጋር አገናኝተው መግለጫ ለማውጣት ብዙም አልቆዩም። ፕሬዝዳንቱ ሐሰን ሸይኽ ማሕሙድ ስልክ አንስተው በርካታ አገራት መሪዎች ጋር ደወሉ። አስመራ የበረሩትም ከዚህ በኋላ ነው።
የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነት፣ በኢትዮጵያን እና ሶማሊያን ውጥረት ጨምሮት ኢጋድ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ያደረገ ነበር። በዚህ የኡጋንዳ ስብሰባ ዐቢይ ባይገኙም፣ የሱማሊያ ፕሬዝዳት በስብሰባው ተሳትፈው አንድ ቀን ለሌላ ጉባኤ እዚያው አድረው ወደ ካይሮ አቅንተዋል።
በባህር ጠረፍ ስምምነት ጉዳይ ሐሰን ሸይኽ ማሕመድ እና ሱማሊያውያን ቁጣቸውን እየገለጹ ቢቆዩም፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ቁጥብ ሆነው ታይተዋል። ስለ ስምምነቱ ከፊርማው አንስቶ ማብራሪያ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሑሴን ከፍ ያለ ድምፀት ያለው ጽሑፍ ያሰፈሩት እንኳን ከሱማሊያ ጋር የወገኑት የግብጹ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ በተናገሩ ጊዜ ነው። ከኢትዮጵያ በኩል ሲስተጋባ የነበረው ተደጋጋሚ አቋም “ማንንም መጉዳት አንፈልግም፤ በጋራ እንጠቀም“ የሚል ነበር።
እንደ ታዛቢዎች የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዲህ ዓይነቱን አቋም እንዲይዙ ያስገደዳቸው ስምምነቱ ዲፕሎማሲያዊ ቅርቃር ውስጥ ስለከተታቸው ነው። የሱማሊያው ሐሰን ጉዞ ያደረጉት አስመራ እና ካይሮ ብቻ ቢሆንም፣ ከአንካራ እስከ ዋሺንግተን የሱማሊያ ሉአላዊነት ሊከበር ይገባል የሚሉ መግለጫዎች ወጥተዋል።
ውጥረቱን ለማርገብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሱማሊያው ፕሬዝዳንት ተደጋጋሚ ስልክ ቢደውሉም ሐሰን አላነሱም። ዐቢይ በዚህ ሳይቆሙ ወደ አገሪቱ መልዕክተኛ ለመላክ እቅድ ይዘው የነበረ ቢሆንም አልተሳካላቸውም። ሐሰን ባስነገሯቸው መግለጫዎች ከኢትዮጵያ ጋር ለመነጋገር ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችውን የመግባቢያ “ውል ትቅደድ“ ብለዋል።
በዚህ መሃል ከቻይና ጋር ተመሳሳይ ውዝግብ ውስጥ የምትገባው ታይዋን ብቻ እውቅና የሰጠቻት ሶማሊላንድ፣ በፕሬዝዳንትዋ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነቱ በአንድ ውስጥ ይፈረማል ብላ ነበር።
ነገር ግን አሁን እንደወጡ መረጃዎች ከሆነ በኢትዮጵያ በኩል የስምምነቱ ዕውን መሆን ቀድሞ ከታቀደለት ፍጥነት እንዲዘገይ እየተደረገ ነው። ዐቢይ እና አማካሪዎቻቸው “እስቲ ጉዳዩን ቆም ብለን ዕንየው“ ብለዋል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የመግባቢያ ስምምነቱን የተከተለው ዲፕሎማሲያዊ ጫና ነው። [አምባ ዲጂታል]