Sunday, September 22, 2024
spot_img

የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሕወሓትን ከአሸባሪነት ለመሰረዝ የሚያስችለውን ልዩ ጉባኤ በነገ እለት ሊያካሔድ መሆኑ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፤ ማክሰኞ መጋቢት 12፣ 2015 – የኢፌዴሪ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሕወሓትን ከአሸባሪነት ለመሰረዝ የሚያስችለውን ልዩ ጉባኤ ነገ ረቡዕ መጋቢት 13 ሊያደርግ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሽብርተኝነት ስረዛውን የሚያካሄደው፤ በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ከአምስት ወር ገደማ በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ነው።

የሕወሓትን ከአሸባሪነት መሰረዝ በተመለከተ፤ የገዥው የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ የፓርላማ አባላት ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 12 ውይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል።

በፓርላማው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከረፋድ ሶስት ሰዓት ጀምሮ የተካሄደው ይህ ስብሰባ ለአምስት ሰዓታት የቆየ ነበር ተብሏል።

በስብሰባው ላይ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እና በፓርላማ የመንግስት ተጠሪው አቶ ተስፋዬ በልጅጌ መገኘታቸው ተገልጿል። በስብሰባው አብዛኛውን መድረክ ይዘው የቆዩት አቶ ሬድዋን፤ የህወሓት ከአሸባሪነት መነሳት ያለውን ፋይዳ ለፓርላማ አባላቱ አብራርተዋል ተብሏል። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ለነገው ጉባኤ ‹‹ማንም አባል እንዳይቀር›› ከሚል ማሳሰቢያ ጋር ጥሪ ተደርጎላቸዋል የተባለ ቢሆንም፤ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር እንደሚደረገው የስብሰባው አጀንዳ አስቀድሞ እንዳልተላከላቸው ተነግሯል፡፡ ነገር ግን በነገው ስብሰባ ህወሓትን ከሽብርተኝነት የሚሰረዝ የውሳኔ ሃሳብ ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን አሸባሪነት የፈረጀው፤ ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት በሚያዚያ 2013 መጨረሻ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ነበር።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img