Thursday, November 21, 2024
spot_img

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችውን የፋይናንስ ድጋፍ እቀባ ልታነሳ መሆኑ ተዘገበ

ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ ቆይቶ በተያዘው ዓመት ጥቅምት ወር መቋጫ ባገኘው የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ጦርነት ከመንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቶ የቆየው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ጥሎት የቆየውን የእርዳታ እና የፋይናንስ ድጋፍ እቀባ ሊያነሳ መሆኑን መስማቱን የዘገበው ፎሬን ፖሊስ ነው፡፡

መጽሔቱ ከባለሥልጣናት ሰምቼዋለሁ ባለው መረጃ መሠረት የባይደን አስተዳደር እቀባውን ማንሳቱን በቅርቡ አዲስ አበባ ያቀናሉ በተባሉት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ አንቶንዮ ብሊንክን በኩል ይፋ ያደርጋል፡፡

በሰሜኑ ጦርነት ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ስታወጣ የቆየችውና በመንግሥት እና ሕወሓት የሠላም ስምምነት ሒደት ከፍተኛ ሚና የነበራት አሜሪካ፤ ጦርነቱ በተጀመረበት 2013 ግንቦት ወር ላይ ነበር የመጀመሪያውን ከፍተኛ የጠባለ እቀባ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የጣለችው፡፡ በዚሁ ወቅት በተጣለው እቀባ የኢትዮጵያና የኤርትራ ባለስልጣናት፣ ወታደራዊና የደኅንነት አባላት፣ እንዲሁም የአማራ ክልል ኃይሎችና የህወሓት አባላት ላይ የቪዛ ዕቀባ ተጥሎባቸዋል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው በትግራይ ክልል ውስጥ የሚካሄደው ግጭት እንዲቆምና የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ እንዲወጡ፣ የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል እንዲሁም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑት ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ያደረገችው ጥረት ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነው፡፡

የአሜሪካ መንግሥት እቀባ ቀጥሎ በታኅሣሥ 2014 ኢትዮጵያ ለ20 ዓመታት ያክል ስትጠቀምበት የነበረው የአጎዋ ከቀረጥ ነጻ እድል እንደተሰረዘም ይታወሳል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት ሻክሮ የነበረ ሲሆን፣ መቶ ሺሕዎችን የቀጠፈው የሰሜኑ ጦርነት መቆም የሁለቱን አገራት ባለሥልጣናት እያቀራረበ ይገኛል፡፡ ከጦርነቱ መቆም በኋላ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአሜሪካ አፍሪካ የመሪዎች ፎረም ላይ ወደ ዋሺንግተን በማቅናት ተሳትፈዋል፡፡

አሁን የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ጥሎት የቆየው የእርዳታ እና የፋይናንስ ድጋፍ የመነሳት ጉዳይ በባይደን አስተዳደር ባለሥልጣናት መካከል መከፋፈል ፈጥሯል፡፡ በጉዳዩ ላይ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ የሆኑት ሞሊ ፊ ያሉበት ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ወደ መደበኛ መንገድ ሊመለስ ይገባል የሚል አቋም ይዟል የተባለ ሲሆን፣ የአገሪቱ የታድኦ ድርጅት ዩኤስኤይድ አስተዳዳሪ ሰማንታ ፖወር ያሉበት ቡድን ደግሞ ትንሽ ይቆይ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ማስተካከል ያለበት ጉዳይ አለ ማለቱ ተሰምቷል፡፡

ጉዳዩን ይፋ ያደርጉታል የተባሉት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶንዮ ብሊንክን ወደ ኢትዮጵያ ሊያቀኑ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡ ብሊንከን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው፣ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ቃል አቀባዩ የተናገሩ ቢሆንም፤ ብሊንከን መቼ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ግን መለስ አልጠቀሱም።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img