Tuesday, December 3, 2024
spot_img

ለትግራይ ተልኮ የነበረው 5 ቢሊዮን ብር በአንድ ሳምንት ውስጥ ወጪ ተደርጎ አልቆ በባንኮች ዳግም የገንዘብ እጥረት ተከስቷል ተባለ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ የካቲት 29፣ 2015 – በትግራይ ክልል በድጋሚ ቅርንጫፎቻቸውን ከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ባንኮች፣ በጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት ለደንበኞቻቸው በቂ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ተብሏል።

ተገልጋዮች ወደ ተለያዩ የባንክ ከቅርንጫፎች ገንዘብ ወጪ ለማድረግ ቢሄዱም፣ ጥቂት ባንኮች የሚያስተዳድሯቸው ውስን ቁጥር ያላቸው ቅርንጫፎች ከሚሰጧቸው አነስተኛ ገንዘብ በስተቀር ተጨማሪ ማግኘት እንዳልቻሉ ሪፖርተር ጋዜጣ የባንክ ኃላፊዎችና ደንበኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።

ከአንድ ወር በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር አድርገውት ከነበረው ውይይት በኋላ በተወሰነው መሠረት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አምስት ቢሊዮን ብር ወደ ትግራይ ክልል ልኮ የነበረ ቢሆንም፣ ገንዘቡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ወጪ ሆኖ እንዳለቀ ተነግሯል።

ባንኮቹ ባላቸው የደንበኛ አገልግሎት ስፋትና በብሔራዊ ባንክ ክፍፍል መሠረት፣ ወደ ትግራይ ከተላከው የአምስት ቢሊዮን ብር ጥሬ ገንዘን ለወጋገንና ለአንበሳ ባንኮች አንድ ቢሊዮን ብር በነፍስ ወከፍ የተሰጠ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ቀሪው ሦስት ቢሊዮን ብር ተሰጥቶት ነበር።

ሥማቸው ያልተጠቀሰ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የትግራይ ዲስትሪክቶች የአንደኛው ሥራ አስኪያጅ የሆኑ ግለሰብ እንደገለጹት፣ ማኅበረሰቡ በችግር ላይ የነበረ እንደመሆኑ፣ ገንዘቡ በተፈቀደ ጊዜ እርሳቸው የሚመሩት ባንክ ተጨማሪ ገደብ ሳይጥል በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ብቻ በቀን ለአንድ ግለሰብ እስከ 50,000 ብር ወጪ ሲያደርግ ነበር።
ኅብረተሰቡ ተገበያይቶበት ገንዘቡ ወደ ባንኩ ተመልሶ እንደሚመጣም በማሰብ ይህን እንዳደረጉ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ በክልሉ ያለው ሁኔታ የንግድ ሥርዓቱን እንዳላስተካከለውና ገንዘቡም ተመልሶ ወደ ባንክ እየገባ እንዳልሆነ ነው ያስረዱት።

አክለውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቀሌ ብቻ ካሉት 24 ቅርንጫፎች ከአንደኛው በስተቀር ሁሉም እርስ በእርስ በኔትወርክ ተሳስረው እየሠሩ መሆናቸውን፣ አብዛኞቹ ቅርንጫፎችም በገንዘብ እጥረት ምክንያት መክፈል እንዳቆሙ ገልጸዋል።

‹‹በጣም ጥቂት ቅርንጫፎች ናቸው አሁን ሁለትና ሦስት ሺሕ ብር እየሰጡ ያሉት፡፡ እነሱም ግዴታ ሆኖባቸው ገንዘብ ወደ ባንክ ከሚያስገቡ ኩባንያዎች ከሚሰበስቡት እያወጡ ነው›› በማለት፣ ቅርንጫፎቹ ከብሔራዊ ባንክ የተሰጣቸውን ገንዘብ ጨርሰው ከገበያው የሚያገኙትን ጥቂት ገንዘብ ብቻ እየከፈሉ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሽያጭ ገንዘብ ወደ ባንክ እያስገቡ ካሉት ጥቂት ድርጅቶች መካከል ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የተወሰኑ የቶታል ኢነርጂ ማደያዎች ብቻ መሆናቸውና ሥራ አስኪያጁ ገልጸው፣ ከእነዚህ ውጪ ሌላ የሚገባላቸው ገንዘብ እንደሌለ ተናግረዋል። ‹‹ጥሬ ገንዘብ አሁንም እንደ ሸቀጥ እየተሸጠ ነው ከተማ ውስጥ፣ ይኼንን የሚመለከተው አካል ካላስቆመው ለእኛ በጣም ፈታኝ ነው የሚሆነው›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተመድቦለት የነበረውን ሦስት ቢሊዮን ብር ከአምስት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አከፋፍሎ የጨረሰ መሆኑን፣ ከመንግሥትና ከግል ሽያጮች የሚገኘው ገንዘብ ካለመምጣቱም በተጨማሪ፣ ኅብረተሰቡ በእምነት ማጣት ጥሬ ገንዘቡን አውጥቶ እንደያዘ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። ‹‹የጥሬ ገንዘብ አያያዝና የንግድ ሥርዓቱ ቢስተካከል አምስት ቢሊዮን ብር በቂ ይሆን ነበር›› ብለዋል።

በመቀሌ ከተማ በተለምዶ ‘ትልቁ ቅርንጫፍ’ የሚባለው ብቻ አገልግሎት ሳያቋርጥ እየሰጠ ያለ ሲሆን፣ ከዚህ ቅርንጫፍ ማውጣት የሚቻለው የገንዘብ መጠንም ሦስት ሺሕ ብር ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹እዚህ ቅርንጫፍ ወረፋው በጣም ረዥም ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
በከተማ ውስጥ ጥሬ ገንዘብ እንደ ሸቀጥ እየተሸጠ እንደሆነና ከመሃል አገር ሳይቀር ሰዎች ገንዘብ ወደ ሌላቸው ሰዎች እያስተላለፉ በኮሚሽን እያስወጡ እንደነበር ገልጸው፣ ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነም ‹‹ዋጋ ያስከፍላል›› ሲሉ ተናግረዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img