Sunday, September 22, 2024
spot_img

የትግራይን ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም በሚመክር ስብሰባ ላይ ሦስት የክልሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሳይገኙ መቅረታቸው ተሰማ

  • በስብሰባው ላይ ጀነራል ጻድቃን ገብረተንሳይም እንዳልተገኙ ተነግሯል

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ የካቲት 22 2015 – የትግራይን ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም በሚመክር ስብሰባ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሳይገኙ መቅረታቸው ተሰምቷል፡፡ ከዛሬ ረቡዕ የካቲት 22፣ 2015 ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው ስብሰባ ጥሪ ቢደረግላቸውም ሳይገኙ የቀሩት ፓርቲዎች የብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና)፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና ውድብ ነጻነት ትግራይ ናቸው፡፡

በትግራይ ክልል አዲስ ይመሠረታል ለተባለው ጊዜያዊ አስተዳደር የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ በሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ የሚመራ ሲሆን፣ ስለ ጉዳዩ ለክል ጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ጊዜያዊ መንግሥቱ የሚተዳደርበትን ሰነድ የማዘጋጀቱ ሥራ እየተገባደደ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

ይህንኑ ተከትሎ በዛሬው እለት በትግራይ ስለ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥቱ ይመክራል የተባለ ስብሰባ የተከፈተ ሲሆን፣ ስብሰባው እስከ ነገ ሐሙስ ድረስ የሚቆይ ነው፡፡ ሕወሓት የሚቆጣጠራቸው የክልሉ መገናኛ ብዙኃን በስብሰባው የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የትግራይ ሠራዊት አባላት፣ የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የተለያዮ አደረጃጀቶች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ መሆናቸውን ዘግበዋል፡፡ ሆኖም የተገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች የትኞቹ እንደሆኑ የተቀሱት ነገር የለም፡፡

በዛሬው ስብሰባ ላይ ሳይገኙ የቀሩት ሦስቱ የትግራይ ክልል ፓርቲዎች ከአስር ቀናት በፊት በጋራ በሰጡት መግለጫ በክልሉ ይመሠረታል በተባለው የሽሽግር መንግሥት ምሥረታ ራሳቸውን ማግለላቸውን አሳውቀው ነበር፡፡ ፓርቲዎቹ ከሒደቱ ራሳቸውን ያገለሉት በኮሚቴው ላይ ገለልተኝነት እና የአሳታፊነት ጥያቄ በማንሳት ነው፡፡ በወቅቱ በተሰጠው መግለጫ አንደኛው ተናጋሪ የነበሩት ባይቶና ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ፀጋ ዘአብ ካህሱ ኮሚቴውን ሕወሓት አቋቁሞታል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው፤ ይህም በፕሪቶሪያ ከተደረገው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት መሠረት ተቀባይነት የለውም ብለው ነበር፡፡

በኮሚቴው ምሥረታ ዙርያ ከተቃዋሚዎች ቅሬታ የቀረበበው ሕወሓት ስለ ጉዳዩ እስካሁን ድረስ በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም፤ በትግራይ ክልል ከሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር አስቀድሞ በሥልጣን መጋራት ዙርያ ከመንግሥት ጋር ለመደራደር መዘጋጀቱን በአመራሩ ጌታቸው ረዳ በኩል አስታውቋል፡፡

በፕሪቶሪያው ስምምነት የሕወሓት ዋንኛ ተደራዳሪ የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት ከፌዴራል መንግሥት ከስምምነት ሳይደርስ ምንም ማድረግ እንደማይቻል በመጠቆም፤ ለመደራደር እየተዘጋጀን ነው ብለዋል፡፡ አቶ ጌታቸው በእነርሱ በኩል ይህ አቋም ቢያዝም የፌዴራል መንግሥት ግን እየተዘጋጀ ይሁን ወይም አይሁን አላረጋገጥኩም ነው ያሉት፡፡

በመንግሥት እና ሕወሓት የፕሪቶሪያ ስምምነት በምርጫ ቦርድ በኩል ምርጫ ተደርጎ የትግራይ ክልል የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ተወካዮች እስከሚመሠረት ድረስ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም ሠፍሯል፡፡

በሚቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተደዳር የፌዴራል መንግሥቱን የሚመራው ብልጽግና፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ክልሉን ሲያስተዳድር የቆየው ሕወሓት ድርሻ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከፓርቲዎቹ መካከል ሕወሓት ከመንግሥት ጋር ጦርነት መግጠሙን ተከትሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት እንደተፈረጀና በምርጫ ቦርድም ከፓርቲነት እንደተሰረዘ ይታወቃል፡፡ የሕወሓት ተወካዮ ጌታቸው ረዳ ወደ ፊት ለመራመድ ሕወሓትን ከሽብር ዝርዝር ጉዳይ በመንግሥት መፍትሔ የሚፈልግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

በሌላ በኩል ባለፈው ቅዳሜ ለንባብ የበቃው የእንግሊዝኛው ሪፖርተር ጋዜጣ የሕወሓት ሰዎች ከመንግሥት ጋር በሚያደርጉት ድርድር የክልሉን ፕሬዝዳንት ቦታ ለራሳቸው ወስደው፣ ምክትል ቦታዎችን ለብልጽግና እና ለተቃዋሚዎች ለመተው ማቀዳቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ዛሬ በትግራይ ክልል እየተካሄደ በሚገኘው ስለ ሽግግር መንግሥት በሚመክረው ስብሰባ ከሢስቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በተጨማሪ የሕወሓትን ጦር ይመሩ የነበሩት ጀነራል ጻድቃን ገብረተንሳይም እንዳልተገኙ ተነግሯል፡፡ የሕወሓት አባል እንዳልሆነ የሚነገርላቸው ጻድቃን በስብሰባው ላይ ለምን እንዳልተሳተፉ የታወቀ ነገር የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img