አምባ ዲጂታል፤ ሰኞ ጥር 1፣ 2015 ― የፌዴራል መንግስቱ እና ሕወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የደረሱበትን የዘላቂ ግጭት ማቆም ስምምነት ተከትሎ የኢትዮጵያን መሬት ለቀው ይወጣሉ ተብለው የሚጠበቁት የኤርትራ ወታደሮች፤ በትግራይ ዘግናኝ ወንጀሎችን መፈጸማቸውን ቀጥለዋል ሲሉ የሕወሓት አመራሩ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ገልጸዋል፡፡
ክንደያ ዛሬ ሰኞ ጥር 1፣ 2015 ረፋድ በትዊተር ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ወታደሮቹ በአድዋ ከተማ ከነዋሪዎች ዘርፈውታል ባሉት ግመል እና አህያ የእቃ ጭነት ሲነዱ የሚያሳይ ፎቶግራፍ አያይዘዋል፡፡ ክንደያ ጨምረውም ወታደሮቹ ቤት ለቤት በመዞር ያገኙትን ሁሉ እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳን ስምምነት ቢደረስም ወታደሮቹ በሌሎችም የትግራይ አካባቢዎች ተመሳሳይ ድርጊት ላይ መሠማራታቸውን ክንደያ ጠቁመዋል፡፡
በሕወሓት አመራሩ በዝርፊያ እና ሌሎችም ዘግናኝ ድርጊቶች ውንጀላ የቀረበባቸው የጎረቤት ኤርትራ ወታደሮች፤ ሁለት ዓመት በዘለቀው የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ጦርነት ወቅት ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው የተዋጉ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ወታደሮቹ በትግራይ በቆዩባቸው ጊዜያት ሁሉ በንጹሐን ላይ ዘግናኝ ወንጀሎችን ፈጽመዋል በሚል በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት እና በሕወሓት ሰዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ ይቀርብባቸዋል፡፡
በጥቅምት ወር በተፈረመው የመንግሥት እና ሕወሓት ስምምነት ወታደሮች ከሕወሃት ትጥቅ መፍታት ገፐን ለጎን የኢትዮጵያን መሬት ለቀው እንደሚወጡ ሠፍሯል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ከቀናት በፊት ወታደሮቹ በተለይ ከአድዋ እና አክሱም ከተሞች በመልቀቅ ወደ ድንበር ከተሞች አቅንተዋል ቢባልም፤ አሁንም ድረስ በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚታዩ መረጃዎቹ ወጥተዋል፡፡
የኤርትራ ወታደሮች አሁንም ድረስ ቀጥለውታል የተባለውን በንጹሐን ላይ ያደርሳል ስለሚባለው በደል የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትም ሆነ የአገሩ መንግሥት ያሉት ነገር የለም፡፡