Sunday, September 22, 2024
spot_img

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ‹ወረራ ለመፈጸም ሲፍጨረጨር ነበር› ያሉትን ኃይል የአገራቸው ጦር ማስታገሱን ገለጹ

አምባ ዲጂታል፤ ሰኞ ታኅሣሥ 24 2015 ― የጎረቤት ኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ‹‹ወረራ ለመፈጸም ሲፍጨረጨር›› ነበር ያሉትን ኃይል የአገራቸው ጦር ማስታገሱን የገለጹት ለፈረንጆቹ ዘመን መለወጫ ለአገራቸው ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡

ፕሬዝዳንቱ በአገራቸው ቴሌቪዥን በተነበበ መልዕክታቸው፤ የኤርትራ ጦር አስታግሶታል ያሉትን ‹‹ኃይል›› ማንነት ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ነገር ግን ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚያዙት ጦር ሁለት ዓመት በቆየውና በቅርቡ በሠላም ስምምነት በተቋጨው የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ጦርነት ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ መዋጋቱ ይታወቃል፡፡ የኤርትራ ጦር አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ መሬት ላይ እንደሚገኝ የሚገለጽ ሲሆን፣ የትግራይ ከተሞች ከሆኑት ሽሬ እና አክሱም ወደ ድንበር እየተጠጋ መሆኑንም የሚያመለክቱ ዘገባዎች የወጡት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነው፡፡

በኢሳይያስ አፈወርቂ የሚመራውና ሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክርሲ እና ለፍትህ የተባለው ፓርቲ የቀድሞው የኤርትራ ሕዝብ ነጻነት ግንባር እና ሕወሓት በኤርትራ እና ኢትዮጵያ ወደ ሥልጣን ከመውጣታቸው አስቀድሞ ከኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግሥት ጋር በተደረገው ጦርነት በትብብር የተዋጉ ቢሆንም፤ ሁለቱም ኃይሎች ወደ ሥልጣን ከወጡ በኋላ በ1990ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት በሺሕዎች የተቀጠፉበት ጦርነት ውስጥ ቆይተዋል፡፡

በጦርነቱ የመጀመሪያ ጊዜያት በኢትዮጵያ መሬት ላይ መኖሩ አለመኖሩ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ መሪዎች ማስተባበያ ሲቀርብበት የቆው ጦሩ፤ በትግራይ ክልል በንጹሐን ላይ ግድያን ጨምሮ በርካታ በደል በመፈጸም በተለይ በሕወሓት በኩል ውንጀላ የሚቀርብበት ነው፡፡ የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ባለፈው ዓመት ጦርነቱ በተጋጋለበት ወቅት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጻፉት ደብዳቤ የኢሳይያስ ጦር ከዚህ ቀደም በጦር ሜዳ የተደረሰበትን ሽንፈት እየተበቀለ ነው ብለው ነበር፡፡

ሆኖም ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ለሕዝባቸው ባስተላለፉት የአዲስ ዓመት መልእክት፤ በተጠናቀቀው የፈረንጆ ዓመት ‹‹በሕዝቡ የሚሞቅ እቅፍ ውስጥ›› ያለ ነው ያሉት የአገራቸው ጦር ‹‹ወረራ ለመፈጸም ይፍጨረጨር›› የነበረን ኃይል በፀረ-ማጥቃት አስታግሷል በማለት፤ በዚህም ኩራታቸው ‹‹ገደብ የለሽ›› እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በሰሜኑ ጦርነት ጅማሮ ላይ የሕወሓት ኃይሎች ሮኬቶችን ወደ አሥመራ ማስወንጨፉ ቡድኑ ለአገሪቱ የደኅንነት ስጋት ስለመሆኑ ኤርትራ እንደ ማሳያ ትጠቅሳለች፡፡ ጦሯ የኢትዮጵያን መሬት ከረገጠ በኋላም ፈጽሞታል በተባለው በደል ምክንያት፤ የአሜሪካ መንግሥት በአገሪቱ ወታደራዊ አመራሮች እና በመንግሥት በሚተዳደሩ ተቋማት ላይ ዕቀባ መጣሉ ይታወሳል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img