Thursday, November 21, 2024
spot_img

በሰላም ንግግሩ “የአማራ ብሔር ይወከል” የሚል ጥያቄ የሚያስተጋቡ የአማራ ፖለቲከኞች ከእንቅስቃሴያቸው እንዲቆጠቡ አብን አሳሰበ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የአፍሪካ ኅብረት በሚመራው የሰላም ንግግር “የአማራ ብሔር ይወከል” የሚል ጥያቄ የሚያስተጋቡ የአማራ ፖለቲከኞች ከእንቅስቃሴያቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰበው ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 12፣ 2015 ባወጣው መግለጫ ነው።

ፓርቲው የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 14 ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የመንግሥትና የሕወሃት የሰላም ንግግር ውስጥ “የአማራ ብሄር ይወከል” የሚለው ጥያቄ “ሕወሃት ድርድሩን በብሄሮች መካከል ወደሚደረግ ድርድር ለማውረድ የሸረበው ሴራ ነው” ብሎታል።

የአብን መግለጫ የመጣው የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ለአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የአሜሪካውን ተወካይ ማይክ ሐመርን ጨምሮ ለሌሎችም በጻፈው ደብዳቤ የአማራ ሕዝብ የድርድር ልዑክ የተባለው ቡድን መመሥረቱን ካሳወቀ በኋላ ነው።

ማኅበሩ ተመስርቷል ያለው ቡድን የቀድሞውን የአማራ ልዩ ኃይል አዛዥ ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ የአብን ተወካይ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ፣ አቶ ቴዎድሮስ ትርፌ እና ዶክተር ወንድወሰን አሰፋን ያካተተ መሆኑን ገልጿል።

ሆኖም አብን ማምሻውን ባወጣው መግለጫ “የአማራ ብሄር በሰላም ንግግሩ ይወከል” የሚል ጥያቄ ያስተጋቡ ፖለቲከኞችን “የአላዋቂና ጎጅ” ካለው እንቅስቃሴያቸው ይቆጠቡ ሲል ነው ያሳሰበው። ፓርቲው ጨምሮም እንዲህ ያለውን ጥያቄ ለአፍሪካ ኅብረት ማቅረብ “በአማራ ሕዝብ ላይ ክህደት መፈጸም ይሆናል” ብሏል።

በሌላ በኩው መንግሥት በሰላም ንግግሩ “የሕወሃትን ትጥቅ መፍታት” ዝቅተኛው ቅድመ ሁኔታ እንዲያደርግ ያሳሰበው አብን፣ መንግሥት አሁን እየወሰደው ያለው የመከላከል የኃይል ርምጃም ሕወሃትን ትጥቅ የሚያስፈታ መሆን አለበት ብሏል። አብን አያይዞም፣ ዓለማቀፍ የሰላም አደራዳሪዎች “በወልቃይትና ራያ የባለቤትነትና ማንነት ጥያቄዎች ውስጥ እጃቸውን እንዳያስገቡ” አሳስቧል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img