Saturday, November 23, 2024
spot_img

የአፍሪካ ኅብረት የፌዴራል መንግሥቱን እና የሕወሓት ባለሥልጣናትን በደቡብ አፍሪካ ለማሸማገል ቀጠሮ መያዙ ተዘገበ

  • ለአሸማጋይነት ሥማቸው ሲነሳ የነበረው የቀድሞዋ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ዶላሚኒ ዙማ ጥያቄውን ሳይቀበሉ መቅረታው ተሰምቷል

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ መስከረም 25 2015 ― የአፍሪካ ኅብረት የፌዴራል መንግሥቱን እና የሕወሓት ባለሥልጣናትን በደቡብ አፍሪካ ለማሸማገል ቀጠሮ መያዙን የአገሩ መገናኛ ብዙኃን ዴይሊ ማቨሪክ በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሕመት ለሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የግብዣ ደብዳቤ ልከዋል፡፡

ድረ ገጹ ተመልክቼዋለሁ ያለውና አምባ ዲጂታል ያገኘው በአፍሪካ ኅብረት እስካሁን ድረስ ማረጋገጫ ያልተሰጠበት ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፤ ፈቂ ማሕመት ለዶክተር ደብረጽዮን የፊታችን እሑድ መስከረም 29፣ 2015 ጀምሮ ለሚካሄደው ሽምግልና ደቡብ ደቡብ አፍሪካ እንገናኝ ማለታቸውን ያትታል፡፡

የድረ ገጹ ዘገባ ሽምግልናው በዋነኝነት የሚካሄደው በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ሲሆን፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፉምዚሌ ምላምቦ ደግሞ ኦባሳንጁን ያግዛሉ፡፡

የፌዴራል መንግሥት እና የሕወሓት ባለሥልጣናት በደቡብ አፍሪካ ለሽምግልና ሊቀመጡ ነው የሚለው መረጃ የመጣው የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ አምባሳደር ማይክ ሐመር ለሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት መፍትሔ ለማበጀት በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት መጀመራቸው መነገሩን ተከትሎ ነው፡፡

ነገ ሐሙስ መስከረም 26፣ 2015 ደቡብ አፍሪካ ይገኛሉ የተባሉት ማይክ ሐመር፤ ቀደም ሲል የነበራቸውን ጉዞ አጠናቀው ዋሽንግተን ላይ በሰጡት መግለጫ፣ በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ጥረት ውስጥ ተጨማሪ አሸማጋዮች የሚካተቱበት ሁኔታን አንስተው ነበር፡፡

ሐመር በኦባሳንጆ መሪነት ለሚካሄደው ጥረት ቀድሞ ሥማቸው በተደጋጋሚ ሲነሳ ከነበረው ከኡሁሩ ኬንያታ በተጨማሪ ደቡብ አፍሪካዊቷ ታዋቂ ፖለቲከኛ እና የቀድሞዋ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ድላሚኒ ዙማን አንስተው ነበር፡፡ ለዚህም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ሙሳ ፈቂ ማሕመት ዙማን እንዲሳተፉ ቢጋብዙም ሳይቀበሉት ቀርተዋል ነው የተባለው፡፡ ማሐመት በእርሳቸው ምትክ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፉምዚሌ ምላምቦን መጋበዛቸውንም ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ባልሥልጣናት በደቡብ አፍሪካ ሊገናኙ ነው መባሉን በተመለከተ ከሁለቱም አካላት ይፋዊ ምላሽ አልተሰጠበትም፡፡ ከዚህ የሁለቱ አካላት ተወካዮች ባለፈው ዓመት መጨረሻ ቀናት በአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር አመቻችነት በጅቡቲ ተገናኝተዋል የሚሉ መረጃዎች ቢወጡም ማረጋገጫ አልተሰጠበትም፡፡

በሚቀጥለው ወር መጨረሻ ሁለት ዓመት የሚደፍነው የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ለበርርታ ሺሕዎች ሞት እና ለሚሊዮኖች መፈናቀል ሰበብ የሆነ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img