አምባ ዲጂታል፤ ቅዳሜ ጳጉሜን 5፣ 2014 ― የአፍሪካ ኅብረት የኦሊሴጉን ኦባሳንጆን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኃላፊነት ማራዘሙን በኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሕመት በኩል አስታውቋል፡፡
ሊቀመንበሩ ዛሬ ቅዳሜ ጳጉሜን 5፣ 2014 በትዊተር ገጻቸው ባሳፈሩት መልዕክት ከኦባሳንጆ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን ያመለከቱ ሲሆን፣ በእርሳቸው ላይ አሁንም ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ሙሳ ፋኪ ማሕመት ከኦባሳንጆ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሰላም እና እርቅ ይመጣ ዘንድ ከሁሉም ወገኖች እና ከዓለም አቀፉ ማኀኅበረሰብ ጋር እያከናወኗቸው ያሏቸውን ሥራዎች እንዲቀጥሉ እንዳበረታቱም ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ተደርገው የተሾሙት ኦባሳንጆ፤ በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል እርቅ ለማውረድ አዲስ አበባ እና መቐለ ከተሞች ሲመላለሱ ቢሰነብቱም በሕወሓት በኩል ቅሬታ ይቀርብባቸዋል፡፡
ሕወሓት በሊቀመንበሩ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ተፈርሞ ከሁለት ወር በፊት ለዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ በጻፈው ደብዳቤም ኦቦሳንጆ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቅርበት እንዳላቸው በመጥቀስ የገለልተኝነት ጥያቄ አንስቷል፡፡
በተያያዘ መረጃ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሕመት አዲስ አበባ የሚገኙትን የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመርን አነጋግረዋል፡፡ ሊቀመንበሩ በቆይታቸው የኢትዮጵያን ግጭት ለመቋጨት ዓለም አቀፍ አጋሮች በአፍሪካ ኅብረት የሚመራውን የእርቅ ሂደት እንዲደግፍ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡