- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀለድ ነጻ የሰበሰበውን ገንዘብ መልሶ ፋይናንስ በማድረግ ከሁሉም ዝቅተኛ አፈጻጸም አስመዝግቧል
አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ነሐሴ 4፣ 2014 ― በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ117.2 ቢሊዮን ብር በላይ ቢሆንም ፋይናንስ የተደረገው 35.5 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
እንደ ባንኩ መረጃ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ቁጥር አራት የደረሰና አሥራ አንድ ባንኮች ደግሞ በመስኮት ደረጃ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አሥራ አንዱ በመስኮት ደረጃ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ባንኮችና ወደ ሥራ የገቡት ሁለቱ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት (ዘምዘምና ሒጅራ) ባንኮች በጥቅሉ ከ117.2 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ሰብስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያለው እንደገለጹት፤ እነዚህ ባንኮች ባሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ልክ ፋይናንስ አላደረጉም፡፡
ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን 117.2 ቢሊዮን ብር ሆኖ ሳለ ለብድር ወይም ለፋይናንስ የተደረገው ግን 35.5 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑ የተሰበሰበውን ገንዘብ መልሶ ፋይናንስ ማድረጉ ላይ (ለብድር ማዋል ላይ) የበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግ የሚያመለክት መሆኑን ማስገንዘባቸውን የሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዙሪያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ገበያ የገቡት ዘምዘምና ሒጅራ ባንኮች እስካሁን 86 ቅርንጫፎችን መክፈታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
አሥራ አንዱና ሁለቱ ባንኮች በጠቅላላው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የከፈቷቸው አካውንቶች ቁጥር ከ11 ሚሊዮን በላይ የደረሰ መሆኑንም ከዳይሬክተሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የወለድ ነፃ የባንክ አልግሎት በመሥራት ደረጃ እየሰጡ ካሉ አሥራ አንዱ ባንኮች ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለውን ተቀማጭ ገንዘብ ያሰባሰበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ እስከ 2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ69.6 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ይህም ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ ባንኮችም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ከተቋቋሙት ባንኮች በእጅጉ ከፍተኛ ብልጫ ያለው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ማሰባሰቡን ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሰበሰበውን ገንዘብ መልሶ ፋይናንስ ከማድረግ (ብድር ከመስጠት) አንፃር ዝቅተኛ አፈጻጸም ያለው መሆኑን የሚጠቁም ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከ 2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ማባሰብ ከቻለው 69.6 ቢሊዮን ብር ውስጥ ፋይናንስ ያደረገው 9.3 ቢሊዮን ብር ብቻ በመሆኑ አጠቃላይ ለፋይናንስ የዋለውን የገንዘብ መጠን አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማት መካከል የሰበሰበውን ተቀማጭ ገንዘብ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ጠንካራ አፈጻጸም በማሳየት በዘርፉ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ኦሮሚያ ኅብረት ስራ ባንክ እንደሆነ ተገልጧል።
ባንኩ እስከ 2014 ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከሰበሰበው 16 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 13.5 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን መልሶ ለብድር እንዲውል አድርጓል፡፡
እንደ ብሔራዊ ባንክ መረጃ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ አሁን ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ ካሉት ዘምዘምና ሒጅራ ባንኮች ሌላ ራሚስ ባንክም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ያገኘ ሲሆን በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተመሳሳይ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው አራተኛው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጠው ሸበሌ ባንክ ነው፡፡ ሸበሌ ባንክ ከሌሎች ከወለድ ነፃ ባንኮች በተለየ መንገድ ተቋቁሞ አገልግሎት ለመጀመር እየተዘጋጀ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡