አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ሐምሌ 27፣ 2014 ― በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኘው የጉራጌ ዞን ራሱን በቻለ ክልል ለመዋቀር ያቀረበውን ጥያቄ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን የዞኑ የኮሚኒኬሽን እና ሚዲያ ቡድን መሪ አቶ ፍቃዱ ዘለቀ ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ክልልን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በክልሉ በተደጋጋሚ እና በየጊዜው የሚነሳውን የክልልነት ጥያቄ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ሰነድ አዘጋጅቶ በየደረጃው ውይይት እያደረገበት መሆኑን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ባለፈው ሳምንት በርካታ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች አዲስ በሚመሰረት ክልል ውስጥ ከሌሎች ጋር ለመደራጀት የቀረበውን ሐሳብ አጽድቀዋል፡፡ አዲስ በሚደራጅ ክልል ለመታቀፍ ውሳኔ ካሳለፉት መካከል ወላይታ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ እና ጋሞ ዞኖች እንዲሁም አማሮ፣ አሌ፣ ቡርጂ፣ ባስኬቶ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክላስተር ይገኙበታል፡፡
በሌላ አዲስ ክልል ለመታቀፍ ደግሞ ስልጤ፣ ሀዲያ፣ ሀላባ፣ ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ ተመሳሳይ ውሳኔ በምክር ቤቶቻቸው ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ እነዚህ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በየምድባቸው በክልልነት ለመታቀፍ ውሳኔ ሲያልፉ በዚያው ክልል የሚገኘው የጉራጌ ዞን ግን እስካሁን ውሳኔውን አላሳለፈም፡፡
በጉዳዩ ላይ ለብስራት ኤፍ ኤም የተናገሩት የዞኑ የኮሚኒኬሽን እና ሚዲያ ቡድን መሪ አቶ ፍቃዱ ዘለቀ ‹‹የህዝቡ ጥያቄ በክልልነት ለመዋቀር›› መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህን ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርበናል ያሉት መሪው፤ ምላሹን እየጠበቁ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ አቶ ፍቃዱ የዞኑ ምክር ቤት እስካሁን በአዲሱ አደረጃጀት ዙሪያ አለመወያየቱንም አክለዋል።
ከዚህ ጋር በተገናኘ በማህበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ዞኑ አዲሱን የክላስተር መዋቅሩን አጽድቋል አላጸደቀም በሚል መረጃዎች እየተሰራጩ መሆኑን ያመለከቱት መሪው፤ መረጃዎቹ ሐሰተኛ መሆናቸውን በመግለጽ በዞኑ አመራሮች ላይ ጫናን ለማሳደር የሚደረግ ነው ብለዋል፡፡