Wednesday, December 4, 2024
spot_img

በትግራይ ክልል የታሠሩ አምስት ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ሲፒጄ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፤ ሐሙስ ሐምሌ 14 2014 ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ፤ የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ያሠሯቸውን አምስት ጋዜጠኞች እንዲፈቱ የጠየቀው ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫው ነው፡፡

ሲፒጄ ከእስር እንዲፈቱ የጠየቀላቸው የትግራይ ቴሌቪዥን ባልደረቦች የሆኑት ጋዜጠኞቹ ኃይለ ሚካዔል ገሠሠ፣ ምሥግና ሥዩም፣ ሐበን ሐለፎም፣ ዳዊት መኮንን እና ተሾመ ጠማለው ናቸው።

ቡድኑ ጋዜጠኞቹን የክል ባለሥልጣናት ‹‹ከጠላት ጋር ተባብረዋል›› በማለት ማሠራቸውን ያመለከተ ሲሆን፣ ጠላት የተባሉት የፌዴራል መንግስት እና ገዥው ብልጽግና ፓርቲ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ የክልሉ መንግሥት ባወጣው ሕግ ‹‹ከጠላት ጋር መተባበር›› ከእድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት ያስቀጣል በማለት መደንገጉንም የሲፒጄ መግለጫ አስታውሷል፡፡

ለመብት ተሟጋቹ ድርጅት መረጃ የሰጠው የቀድሞ የክልሉ ቴሌቪዥን ባልደረባ ኢሳቅ ወልዳይ አምስቱ ጋዜጠኞች ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤት ቢቀርቡም የፍርድ ሂደታቸው ምን እንደደረሰ የታወቀ ነገር የለም ብሏል፡፡

አሁን ከታሠሩት ጋዜጠኞች መካከል መከላከያ ባለፈው ዓመት ትግራይን ተቆጣጥሮ ጊዜያዊ አስተዳደር በተቋቋመበት ወቅት ሐበን ሐለፎም በዜና አንባቢነት፣ ተሾመ ጠማለው በዓለም አቀፍ እና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ክፍል ዳይሬክተርነት እና ዳዊት መኮንን በፊልድ ሪፖርተርነት ሠርተዋል፡፡ እነዚህ ሦስት ጋዜጠኞች ከመታሠራቸው ጥቂት ወራት ቀደም ብለው ከሥራ ታግደው እንደነበር መስማቱንም ቡድኑ ገልጧል።  

በጉዳዩ ላይ የተናገሩት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የሲፒጄ ተወካይ የሆኑት ሙቶኪ ሙሞ በትግራ ክልል የሚሠሩ ጋዜጠኞች ያለ ፍርሃት እንዲሠሩ መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የጋዜጠኞቹን እስር በተመለከተ ሲፒጄ ለሕወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ፣ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት እና ለትግራይ ቴሌቪዥን ጥያቄ ባቀርብም ምላሽ አላገኘሁም ብሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img