Sunday, September 22, 2024
spot_img

መንግሥት ሕወሓት ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ ለማስገባት እየሠራ ነው ሲል ከሰሰ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ግንቦት 24 2014 ያለፉትን 19 ወራት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ የቆየት ሕወሓት፤ ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ ለማስገባት እየሠራ ነው በሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡

ይህንኑ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ከሆነ ሕወሓት በቅርብ ጎረቤት ኤርትራን እየተነኮሰ ኢትዮጵያን ጦርነት ውስጥ ለማስገባት ነው፡፡

የለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) ክስ የመጣው ሕወሓት በቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ በኩል ሰኞ ግንቦት 22፣ 2014 በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜ እና እሑድ የኤርትራ ሠራዊት በሽራሮ ከተማ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል መባሉን ተከትሎ ነው፡፡ ቃል አቀባዩ የኤርትራ ሠራዊት ከአንድ ሳምንት በፊት ግንቦት 16፣ 2014 በ57ኛ እና 21ኛ ክፍለ ጦሮቹ ወደ ትግራይ ክልል ጥቃት ሠንዝሮ አዲአዋላ በተባለው አካባቢ የትግራይ ክልል ኃይሎች ጥቃቱን እንደመከቱት ገልጸዋል።

የኤርትራ ጦር ሠንዝሮታል የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ከራሱ ከኤርትራ መንግሥት የተሰጠ መረጃ ባይኖርም፣ ሬውተርስ ተመልክቼዋለሁ ያለውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰነድ ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ፣ የኤርትራ ጦር ቢያንስ 23 ጊዜ ወደ ሽራሮ ከባድ መሣሪያ ተኩሷል፡፡

የዜና ወኪሉ የኤርትራ ሠራዊት በሽራሮ ከተማ ላይ ከፍቶት ነበር በተባለው ጥቃት፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ተጠልለውበት የነበረ ትምህር ቤት ጉዳት ደርሶበታል ብሏል።

ተሰንዝሯል የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ለአል ዓይን የተናገሩት የፌዴራል መንግሥት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር)፤ ትንኮሳውን ቀድሞ ያደረገው ሕወሓት እንደሆነና በዚህም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ ሕወሓቶች በጥቃቱ ጉዳት እንዳስተናገዱ በመግለጽ ‹‹ሬሳ እንኳን መንሳት አልቻሉም፤ በጣም ብዙ ሰው ወድሞባቸዋል›› ብለዋል፡፡

አል ዓይን በሕወሓትና በኤርትራ መካከል ያለው መካረርና አልፎ አልፎ እየተደረገ ያለው ውጊያ፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ወደ ጦርነት ሊያስገባ አይችልም ወይ በሚል ለሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርቤላቸው፤ ወደዚያ የሚያመራ ሁኔታ እንደሌለ ነግረውኛል ብሏል፡፡ ሕወሃት ትንኮሳውን የሚፈፅመው ሁለቱን ሀገራት ወደ ግጭት ለማስገባት እንደሆነ የገለጹት ለገሠ ቱሉ፣ ይህ ግን መቼም ቢሆን ‹‹አይሳካም›› ማለታቸው ተመላክቷል፡፡

ከተጀመረ 19 ወራት ያስቆጠረው የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ጦርነት አሁን በሕወሓት ጥቃት ሰንዝሮብኛል በሚል የተከሰሰውን የኤርትራን መንግሥት ያሳተፈ ሲሆን፣ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ናይጄሪያዊው ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በተደጋጋሚ አዲስ አበባ እና መቀሌ ሲመላለሱ መሰንበታቸው ይታወቃል፡፡

ኦባሳንጆ ባለፉት ጊዜያት ድምጻቸውን አጥፍተው ቆይተው ትላንት ግንቦት ዳግም መቀሌ መገኘታቸውን የሕወሓት ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል፡፡ አቶ ጌታቸው በትዊተር በማስታወሻቸው ‹‹ከቀጠናዊ ጉዳዮች ጋር ለመምከር ዛሬ ፕሬዝደንት ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሳንጆን ተቀብለዋል›› ከማለት ውጪ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img