አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ግንቦት 14፣ 2014 ― የፌዴራል መንግሥቱ የኮሚኒኬሽን አገልግሎት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ሕወሓት የመከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ በወጣበት ወቅት አግቶ ያቆያቸውን የሠራዊቱን ቤተሰብ አባላት ምርኮኛ በሚል መልቀቁን አስታውቋል፡፡
የኮሚኒኬሽን አገልግሎቱ መግለጫ የመጣው ሕወሓት ሐሙስ ግንቦት 11፣ 2014 በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተማረኩ ናቸው ያሏቸውን ከ4 ሺህ በላይ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን በምህረት እለቃለሁ ማለቱን ተከትሎ ነው፡፡
በህወሓት የሚተዳደረው የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው፤ በምህረት ይለቀቃሉ የተባሉት ወታደሮች ለቀይ መስቀል ተላልፈው ይሰጣሉ ተብሎ ነበር፡፡
ነገር ግን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን በሃሰተኛ መረጃና ፕሮፖጋንዳ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የሚደረግ ጥረት ቦታ የለውም የሚል ርእስ በሰጠው መግለጫው ‹‹የሽብር ቡድን›› ሲል የጠራው ሕወሓት ‹‹የአማራና አፋር አካባቢዎችን በሃይል ወረራ ስር አደርጎ በቆየባቸው ወቅቶች በግዳጅ ይዞ ኢሰብአዊ ተግባራትን ሲፈጽምባቸው የነበሩ ሰዎችንና ለራሱ ፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ለማዋል ምርኮኛ በማለት የሃገር ውስጥም ሆነ አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማጭበርበር እየሞከረ ነው›› ብሏል፡፡
መግለጫው መንግሥት ጉዳዩን አስመልክቶ እያደረገ ባለው ማጣራት ‹‹ምርኮኞች›› ናቸው ተብለው የተለቀቁት አብዛኞቹ ዜጎች የመከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ በወጣበት ወቅት በሽብር ቡድኑ ታግተው የቀሩ የሰራዊቱ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው እንደታወቀ አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ከልዩ ልዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ለስራ ትግራይ ክልል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሲቪል ነዋሪዎችን አግቶ የቆየው ቡድኑ፤ አሁን የፖለቲካ ትርፍ አገኝበታለሁ ባለው የፕሮፖጋንዳ ድራማ የመከላከያንና የተለያዩ ጸጥታ ሃይሎችን መለዮ በማልበስ በምርኮኛ ሥም አሰልፏቸዋል ሲል ምርኮኛ የተባሉትን ሰዎች ምርኮኛ እንዳልሆኑ ገልጧል።
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ‹‹ሕወሓት ከሰሞኑ የጦርነት ክተት እያወጀና በይፋም እየተዘጋጀ መሆኑን ማስታወቁን ተከትሎ ያለችውን እንጥፍጣፊ ስንቅ ወደ ጦርነት ለማዞርና ለዳግም ጥፋት ራሱን እያዘጋጀ ለመሆኑ የአሁኑ ድርጊቱ ሁነኛ ማሳያ ነው›› ሲል አትቷል፡፡
በተጨማሪም የሕወሓት ተባባሪ ናቸው ካላቸው ሸኔ ሲል የሚጠራ ቡድን እና ሌሎችም ታጣቂ ቡድኖች የዚህ ፕሮፖጋንዳ ተባባሪዎች ናቸው ያለው መግለጫው፣ ሕወሓት ከእነዚህ ቡድኖች አባላትን በመመልመልና በማሰባሰብ ከሸኔ የሽብር ቡድን ጋር በጋራ ሲያሰለጥናቸው የነበሩ ሰርጎ ገብ ሃይሎችንም በምርኮኛ ስም አደራጅቶ የእኩይ ተልእኮው ማስፈጸሚያና መረጃ መቀበያ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው ብሏል፡፡
ሕወሓት ምርኮኛ ናቸው ያላቸውና በፌዴራል መንግስቱ አይደሉም የተባሉትን ሰዎች አስመልክቶ ከሁለት ቀናት በፊት በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የመቀለ ምርኮኞች ማዕከል አስተባባሪ ናቸው ተብለው የቀረቡት ብርሃነ በቀለ ሰዎቹ የትግራይ ኃይሎች እስከሚቆጣጠሩት አካባቢ በመኪና ተጓጉዘው ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ተላልፈው እንደሚሰጡ ገልጸው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር የአፍሪካ ቃል አቀባይ አሊዮና ሲዬንኮ፤ ‹ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማሕበር በእዚህ ኦፕሬሸን ውስጥ ተሳታፊ አይደለም›› ሲሉ ምላሽ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡
በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች ተዛምቶ በነበረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ካስከተለው ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ በተጨማሪ፤ በሁለቱም ወገን ያሉ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የሠራዊት አባላት ምርኮኛ እንደሆኑ ይታመናል።