አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ግንቦት 3፣ 2014 ― በኢትዮጵያ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ለማርገብና ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሆኑት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት እና የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን መሠረታዊ አቅርቦቶን ማትም ዘይት፣ ስኳርና ስንዴን በዱቤ ከውጭ እንዲያስገቡ መንግሥት ፈቅዶላቸዋል፡፡
ይህንኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ትላንት ግንቦት 2፣ 2014 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
መንግሥት የዱቤ ወይም ዲፈርድ ሌተር ኦፍ ክሬዲት አሠራርን ሲጠቀም መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎችን እንዲገቡ በማድረግ ባለፈው ወር 43 በመቶ የደረሰውን የምግብ ዋጋ ግሽበት ለማርገብ አስቧል ነው የተባለው፡፡
መንግሥት ከዚህ ቀደም መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን አቅርቦት ለመጨመር በማሰብ የፍራንኮ ቫሉታ አሠራርን እንዲሁም ሸቀጦች ያለ ተጨማሪ ዕሴት ታክስ እንዲገቡ ፍቃድ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ የተደረጉት ማስተካከያዎች ዋጋ ግሽበት ከመቀነስ አኳያ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አላመጡም፡፡
አሁን የተፈቀደውን አሠራር በተመለከተ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢና ቺፍ ኢኮኖሚስት የሆኑት አቶ ፍቃዱ ድጋፌ ለስኳር ምርት ዱቤው የሚከፈልበት ጊዜ ሁለት ዓመት መሆኑን፣ ለስንዴና ዘይት በአንድ ዓመት ውስጥ ሊከፈል እንደሚገባ መናገራቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ይህን መሰል አሠራር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፣ አገር ውስጥ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር አይገናኝም ብለዋል፡፡ አሠራሩም የሚመራው የአቅርቦት ብድር (ሳፕላይ ክሬዲት) መመርያ ሲሆን፣ ለተግባራዊነቱ ብሔራዊ ባንክ አቅጣጫ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራት በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ግብዓት ማስመጣት ባለመቻላቸው መዘጋታቸው ሲነገር፣ ለአብነትም ከ20 በላይ የታሸገ ውኃ ምርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ይጠቀሳሉ፡፡