Friday, November 15, 2024
spot_img

ኢንዶኔዥያ የፓልም ዘይት ወደ ውጭ እንዳይላክ አገደች

አምባ ዲጂታል፤ ዐርብ ሚያዝያ 21 2014 ― በዓለም ከፍተኛ መጠን ያለው የፓልም ዘይት ወደ ውጭ ከሚልኩ አገራት ቀዳሚዋ የሆነችው ኢንዶኒዥያ፣ ወደ ውጭ የምትልከውን ዘይት አግዳለች፡፡ አገሪቱ እገዳውን የጣለችው የአገር ውስጥ ፍጆታዋን ለማርካት የሚል ምክንያት በማስቀመጥ ነው፡፡

ኢንዶኒዥያ በተለይ በአገሯ የምግብ ዘይት ዋጋ መናር ስላሳሰባት ማንኛውም የምግብ ዘይት መሥሪያ የሚሆን ጥሬ የሰብል ምርቶች ላልተወሰነ ጊዜ ለውጭ ገበያ ዝግ ሆነው እንዲቆዩ ጥብቅ መመሪያ ማስተላለፏ ነው የተነገረው፡፡

የኢንዶኒዥያ የፓልም ዘይት ዕቀባ የመጣው በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት የተነሳ የሱፍ አበባ ዘይት ገበያ መናጋቱን ተከትሎ ነው፡፡ አሁን ጦርነት ላይ ከሚገኙት መካከል ዩክሬን በዓለም ቁጥር አንድ የሱፍ አበባ ዘይት አምራችና ላኪ አገር የነበረች ሲሆን፣ በየዓመቱ 5 ሚሊዮን ቶን ለዓለም ታቀርብ ነበር፡፡ ሩስያ በበኩሏ የዓለምን 25 ከመቶ የሱፍ ዘይት ምርት የምትሸፍን አገር ነበረች፡፡

አሁን ላይ ኢንዶኒዥያ በፓልም ዘይት ላይ የጣለችው የውጭ ንግድ ዕቀባ ለአፍሪካ ነዋሪዎች ትልቅ ራስ ምታት እንደሚሆን ተፈርቷል መባሉን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በተለይ ከዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ የዋጋ ግሽበት መከሰት፣ ብሎም የነዳጅና የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መናር ትልቅ ፈተና በሆነበት ወቅት የዘይት እጥረት መከሰቱ ነገሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገዋል ተብሏል፡፡

የፓልም ዘይት የተለያዩ የአትክልት ዘይቶችን ለማዘጋጀት የሚረዳ ሲሆን፣ ከርሱ ሌላ ለጽዳትና የመዋቢያ ምርቶች መሥሪያነት ይውላል፡፡

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ርካሽ የሆነው የፓልም ዘይት ተጠቃሚ ናቸው፡፡ አፍሪካ ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት ብቻ በድምሩ በገንዘብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት፣ በመጠኑ 4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚሆን የፓልም ዘይት ከኢንዶኒዥያና ማሌዢያ አስገብታለች፡፡

የኢንዶኒዥያን የውጭ ንግድ ዕቀባ ተከትሎ የአውሮፓ አገራት የሆኑት ስፔን፣ ቱርክ፣ ጀርመንና ዩኬ በአንዳንድ መደብሮች ዘይት ለሁሉም በፍትሃዊነት እንዲዳረስ በሚል በነፍስ ወከፍና በቤተሰብ የተወሰነ ምርት ብቻ መሸጥ መጀመራቸው ተሰምቷል፡፡

በኢትዮጵያም በቅርቡ በተመሳሳይ የዘይት ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img