Friday, November 15, 2024
spot_img

የገንዘብ ሚኒስቴር 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለመግዛት የተፈጸመ ስምምነት የለም ማለቱ ተዘገበ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ የካቲት 30 2014 ― የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለመግዛት የተፈጸመ ስምምነት የለም ያለው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ንግድ ቢሮዎች ጋር በመሆን የካቲት 28፣ 2014 በአገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰተው የምግብ ዘይት ዋጋ መናር ለመፍታት የሚያግዝ 40 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ለመግዛት ስምንት መፈጸሙን ማሳወቁን ተከትሎ ነው፡፡

በወቅቱ የሚኒስቴሩ የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ወ/ሮ መስከረም ባሕሩ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት እያንዳንዳቸው 20 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በልዩ ሁኔታ እንዲያስገቡ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረው ነበር፡፡

ዳይሬክተሯ መበደበኛ የግዥ ሒደቶችን መከተል ወራትን ሊወስድ ስለሚችል በልዩ ሁኔታ የሳዑዲ ዓረቢያ አስመጪ ድርጅት መመረጡንና የካቲት 28፣ 2014 ስምምነት መፈጸሙን ሪፖርተር ጋዜጣ እንደነገሩት ዘግቧል፡፡ በዓለም ላይ ያለው የምግብ ዘይት ዋጋ የሚታወቅ በመሆኑ አስመጪ ድርጅት መመረጡ ችግር እንደማይፈጥርም አክለዋል፡፡

ሆኖም ጋዜጣው ወ/ሮ መስከረም በጉዳዩ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ ከሆኑት አቶ ኤፍሬም ተሰማ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት እንደሚቻል ቢጠቁሙም፣ አማካሪው ከዚህ ተቃራኒ ነግረውኛል ብሏል፡፡ እንደ አቶ ኤፍሬም ዘይት ለማቅረብ የተመረጠም ሆነ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ያደረገ አቅራቢ የለም፡፡ መንግሥት ሊያስገባ ያሰበው የዘይት መጠንን በተመለከተም፣ ውሳኔ ላይ እንዳልተደረሰና ጉዳዩ በጥናት ላይ ያለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ምን ያህል ነው የሚለውን እያጠና ነው፡፡ ይህንን ጥናት ደግሞ በሚቀጥለው ሳምንት ነው የምንጨርሰው፤››  ያሉት አማካሪው፣ የሚገባው ዘይት መጠን የሚታወቀው ከጥናቱ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በገንዘብና በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴሮች እየተደረገ ያለው ጥናት የአገሪቱን ፍላጎት መጠን፣ እንዲሁም ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦትና የጉድለት መጠን እንደሚዳስስና ከጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ እንደሚሰበስብ ታውቋል፡፡ ከምግብ ዘይት ፈላጊዎች ውስጥም ቢሆን እንደ የኑሮ ደረጃቸው ፈሳሽና ፓልም ዘይት ተጠቃሚዎችን መለየት እንዳለባቸው አቶ ኤፍሬም አብራርተዋል፡፡

በሰኞ ዕለት መግለጫ ላይ የተገኙት አዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ፣ የዋጋ ጭማሪው የተከሰተው መንግሥት በድጎማ ለኅብረተሰቡ በሚያሠራጨው የፓልም ዘይት ላይ ብቻ ሳይሆን በተለምዶ ፈሳሽ ዘይት በሚባለው ጭምር ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ የዋጋ ጭማሪ እንደሚታይ ያስረዱት አቶ መስፍን፣ ነገር ግን መንግሥት በሚያሠራጨውና በአገር ውስጥ አምራቾች ተመርቶ በሚቀርበው የዘይት ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዳልተደረገ ገልጸዋል፡፡ ከተማዋ ከፊቤላና ከሸሙ የግል ዘይት አምራቾች፣ እንዲሁም ከንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሚገኝ በአጠቃላይ ሰባት ሚሊዮን ሊትር ዘይት በቅርብ ቀናት ውስጥ እንደምታገኝ አቶ መስፍን አስታውቀዋል፡፡

የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተሯ ወ/ሮ መስከረም በበኩላቸው፣ የምግብ ዘይትን ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የአገር ውስጥ ፍላጎትና የሚያስፈልገውን መጠን ከእነ መፍትሔው የሚያጠና ቡድን መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪው አቶ ኤፍሬም የዘይት ግዥን አስመልክቶ የሚደረገው ጥናት በሚቀጥለው ሳምንት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ በማስረዳት፣ ግዥውን ለመፈጸም ጨረታ ወይስ ሌላ አማራጭ ይወሰድ የሚለውን በተመለከተም ውሳኔ ላይ አለመደረሱን ገልጸዋል፡፡ የሚገዛው የዘይት መጠን በጥናቱ ውጤት ላይ የሚመሠረት ቢሆንም፣ ከ40 ሚሊዮን ሊትር ሊበልጥ እንደሚችል አክለዋል፡፡ ሰማኒያ በመቶ የሚሆነውን የምግብ ዘይት ፍጆታዋን ከውጭ በምታስገባው ኢትዮጵያ፣ ካለፈው ሳምንት ወዲህ በችርቻሮ በምግብ ዘይት መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img