አምባ ዲጂታል፤ ማክሰኞ የካቲት 22፣ 2014 ― መንግሥት አሸባሪ የሚለው ሕወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ቡድናቸው ከበርካታ አገራት ጋር ግንኙኑት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው ሕወሓት በሚቆጣጠረው ትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ይህንኑ የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ አገራቱ የትኞቹ እንደሆኑ ከመዘርዘር ተቆጥበዋል፡፡ ቃል አቀባዩ እንደ አገር የሚቆጥረን ስለሌለ አገራቱም ከትግራይ ጋር ግንኙነት አለን ብለው ይፋ ሊያደርጉን አይችሉም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ነገር ግን በትግራይ ጦርነት ለፌዴራል መንግስት ድጋፍ ሰጥታለች ከምትባለዋ የተባለው ዐረብ ኤምሬቶች በኩል ግንኙነት የመፍጠር ፍላጎት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የትግራይን ሕልውና አስተማማኝ መሠረት ላይ ለማረጋገጥ ‹‹ጠላት ቀንሰን ወዳጅ ማብዛት አለብን›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ግንኙነት መፍጠር ትፈልጋለች ያሏትን የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶችን ‹‹በድላችሁናል እንላችኋለን፤ ከጠላት ጋር አብራችሁ ቀጥቅጣችሁናል እንላቸዋለን፣ ከዚያ መድሃኒት እናመጣለን ይላሉ፣ መድሃኒት ያስፈልገናል፣ ስለዚህ አኩርፈናል ብለን ልንተወው አንችልም›› ብለዋል፡፡
አቶ ጌታቸው አሁን የትግራይን ሙሉ አቅም ማንቀሳቀስ አለብን ያሉ ሲሆን፣ በዲፕሎማሲ ዘርፍ ተሰሚነታችንን ከፍ የማድረግ ሥራ እንሰራለን ሲሉ ቀጣይ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ንግግር በተመለከተም አቶ ጌታቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር ከወሓት ጋር ስለሚደረግ ድርድር ጥያቄ ቀርቦላቸው ‹‹እስካሁን የተደረገ ድርድር የለም፤ እስከዚህ ደቂቃ ድረስ›› የሚል ቀጥተኛ ምላሽ ሰጥተዋል። በዚሁ ምላሽ ወቅት ‹‹ስለድርድር ብዙ ሲወራ እሰማለሁ፤ ግን እስካሁን ድርድር አልተደረገም። አልተደረገም ማለት ግን እስከነአካቴው ድርድር የሚባል ነገር አይኖርም ማለት አይደለም›› ሲሉ ድርድር ሊደረግ የሚችልበት ዕድል መኖሩን ጠቁመው ነበር። ዐቢይ ‹‹የሰላም አማራጭ ካለ፣ ሕወሓት ቀልብ ከገዛ፣ በጦርነት እንደማያዋጣው እንደማያሸንፍ ከተገነዘበ፤ እኛ በደስታ ነው የምናየው›› ሲሉ መንግስታቸው ለድርድር ያለውን ዝግጁነት ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል።
በእለቱ የነበረውን ይህን ንግግር በተመለከተ የሕወሓት ቃል አቀባዩ በፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ‹‹በቋንቋ ደረጃ ተቀይሮ መምጣቱም አንድ ነገር ነው›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ያልተለመዱ የሚመስሉ ነገሮች አሉ፡፡ የትግራይ ሕዝብ በዚህ ጦርነት ከማንም በላይ ተጎድቷል ማለታቸውን መልካም ነው፡፡ ይህ መታመኑም ትልቅ ነገር ነው›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ‹‹የትግራይ ሕዝብም ቢሆን ከሰላም ይጠቀማል ብለን ስለምናስብ፤ የሰላም እድል ካለ ከመጠቀም ወደኋላ አንልም፤ በኛ በኩል ጦርነት ያዋጣል ብለን አናምንም›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት ‹‹ጠመንጃ ዘቅዝቆ መቀመጥ›› እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ጌታቸው አሁንም ‹‹የትግራይን ሕዝብ ለማንበርከክ›› ይደረጋል ያሉት እንቅስቃሴ ጋብ እንዳላለ ተናግረዋል፡፡
ለሰላም እንቅስቃሴው እንቅፋት ሆነዋል በማለት ተጠያቂ ያደረጉት ‹‹የአማራ ተስፋፊ›› ያሉትን ኃይል እና በትግራይ ጦርነቱ ተሳትፎ ያደረገውን የኤርትራ መንግስት ነው፡፡ አቶ ጌታቸው እነዚህን አካላት ‹‹የጦርነት ባለጸጎች ናቸው›› ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡
በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት መካከል የሚደረገው ጦርነት ከጀመረ አስራ አምስት ወራት ተቆጥረዋል፡፡